ኮርፖሬሽኑ በባሌ ዞን ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ በባሌ ዞን ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ

የካቲት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በክልሉ ባሌ ዞን የድርቅ አደጋን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ዘንድሮ በዞኑ የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።
በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት መቋቋም የሚያሥችሉ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ክፍሉ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ በዞኑ ሁለት ትላልቅና ሶስት የአነስተኛ የመስኖ ግድቦች ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ነው።
ግንባታቸው እየተከናወነ ከሚገኙት ውስጥ የሶስቱ አነስተኛ የመስኖ ግድቦች ወጪ 700 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ጠቁመዋል።
የተከሰተው ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የእነዚህን ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በተመሳሳይም ኮርፖሬሽኑ ከሌሎች የግንባታ ተቋራጮች ጋር በመሆን በዞኑ የሚገነቡ ሁለት ትላልቅ የመስኖ ግድቦች ግንባታ ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
ሁለቱ ግድቦች ራይቱና ደሎ መና በተባሉ የዞኑ አከባቢዎች የሚገነቡ ወልመል እና ጨልጨል የሚባሉ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በደሎ መና አከባቢ ግንባታ ላይ የሚገኘው ወልመል የመስኖ ፕሮጀክት 11ሺ ሔክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
ግድቡ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስም 5ሺ ሔክታር መሬት ማልማት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸው፤ ቀሪውን 6ሺ ሄክታር መሬት የሚያለማው የግንባታ ምዕራፍ ደግሞ በቀጣይ ዓመት የሚጠናቀቅ ይሆናል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የጨልጨል የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የመስኖ ቦይ ዝርጋታ ስራ ውል ውስዶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም ገልጸዋል።