በኦሮሚያ ክልል ለ976 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ተመቻቸ

88

የካቲት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ እስካሁን ለ976 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል የተመቻቸላቸው መሆኑን የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

የስራ ዕድሉ የተመቻቸው በበጀት ዓመቱ  ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ ነው።

የቢሮው አመራርና ሰራተኞች  በሰበታ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስምንት ወራት ሲከናወኑ የቆዩትን የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራትን በተመለከቱበት ወቅት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ማቲዮስ ሰቦቃ እንዳሉት፤ የጉብኝቱ ዓላማ  በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ወደ መካከለኛና አነስተኛ የተሸጋገሩ ማህበራት  በሚባለው ልክ መስራታቸውን ለማረጋገጥ ነው።

በጉብኝቱ የተከናወኑ ተግባራትን ከማየት ባለፈም በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት በተለይም በአምራች ዘርፉ በአንድ ከተማ የተሰራን ለሌላውም እንደ መልካም ተሞክሮ በማስፋት ለሀገር የሚጠቅም ውጤት የሚመዘገብበትን እድገት ማምጣት ነው ብለዋል።

በክልሉ በተያዘው የበጀት ዓመት  ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን  ለ976 ሺህ ወጣቶች በቅጥር፣ በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀት የስራ ዕድል  መመቻቸቱን  አቶ ማቲዮስ አስታውቀዋል።

የሰበታ ከተማ አስተዳደር  ስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ታምሬ በበኩላቸው ፤ በአስተዳደሩ ከተደራጁ ዓመት ሳይሞላቸው በምርታቸው የገበያ ተፎካካሪ መሆን  የቻሉትን ማህበራት ተሞክሮ ማስፋቱ ላይ እየሰራን ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በህገወጥነት የተያዙትን ጨምሮ ከ300 በላይ ሼዶች  ለአዳዲስ ስራ አጦች መስጠታቸውን ያወሱት አቶ ወንድወሰን፤ አሁንም ወደ 15  ሼዶች ለተመሳሳይ ተግባር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበሩትን ሼዶች  2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በመመደብ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በሮቻቸውን  ገጥሞ ወደ ስራ በመመለስ ለተጠቃሚዎች እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

 እነ ተሾመና ጓደኞቹ የፕላስቲክ ማምረቻ ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ተሾመ ሃይሉ በሰጠው አስተያየት፤ ከኦሮሚያ ካፒታል ሊዝ ብድር መነሻ ማሽን ገዝተው የውሃ ማስተላለፊያ ፕላስቲክ እንደሚያመርቱ ጠቅሶ፤

"የእኛ መነሻ ገንዘብ ሳይሆን በጭንቅላታችን ይዘን የመጣነው የትልቅነት ፕሮፖዛል ነው" ብሏል።

ግባቸውን ደግሞ ስራቸውን  ማስፋፋትና በዚህም ለተማረው የሰው ሃይል ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደሆነም ገልጿል።

በጨርቃጨርቅ ስፌት ስራ፣ በፈሳሽ ሳሙና ምርት፣ በዶሮ እርባታና ከብት እርባታ የተሰማሩት ማህበራት   እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ተመልክቷል።

ብድርና የገበያ ትስስሩ የበለጠ ቢመቻችላቸው በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉም ማህበራቱ ጠቁመዋል።

የሰበታ ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ  ከሃያ ሺህ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገበት አቅዶ እስካሁን ከዕቅድ በላይ መከናወኑና 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር እንዳመቻቸላቸው  ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም