የቤንዚን እጥረት በሥራችን ላይ ችግር ፈጥሮብናል-አሽከርካሪዎች

73

ጋምቤላ የካቲት 29/2014(ኢዜአ)በጋምቤላ ከተማና አካባቢው የተከሰተው የቤንዚን እጥረት በሥራቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን አሽከርካሪዎች ገለጹ።

የቤንዚን እጥረት የተከሰተው በአንዳንድ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ምክንያት መሆኑን የክልሉ ንግድና ኢንድስትሪ ቢሮ አስታውቋል።

በጋምቤላ ከተማ ‘‘የባጃጅ’’ና የሞተር አሽከርካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው የሚገኙ ማደያዎች የሚያመጡትን ነዳጅ ለሽያጭ እያቀረቡ ባለመሆናቸው ሥራቸውን ለማከናወን አልቻሉም ።

"ማደያዎቹ  ነዳጁን ለጥቁር ገበያ አሳልፈው በመስጠት እጥረት እንዲከሰት ያደርጋሉ" ብለዋል።

ከአሽከርካሪዎች መካከል አቶ ውቤ ምህረቱ በሰጡት አስተያየት ለባጃጅ ፍጆታ የሚሆን ነዳጅ በበቂ ሁኔታ ባለማግኘታቸው ተገቢውን አገልግሎት ስለማያገኙ በኑሯቸው ላይ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

አንዳንድ ስግብግብ ግለሰቦች ከማደያዎች በበርሜል ገዝተው አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 150 ብር እየሸጡ እንደሚገኙ ገልጸው፡ የሚመለከተው አካል በግለሰቦቹ ላይ እርምጃ ሲወሰድባቸው እንደማይታይ ተናግረዋል።

መንግሥት የነዳጅ አቅርቦት ችግር እንደሌለ እየገለጸ ቢሆንም በአካባቢያቸው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት መኖሩን የገለጹት ደግሞ የሞተር  ቢስክሌት አሽከርካሪ አቶ ኮር ጀሽዋ ናቸው።

"ችግሩ ያለው በማደያዎች አካባቢ ይመስለኛል" ሲሉ ጠቁመዋል ።

የባሮ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም በለጠ በበኩላቸው የነዳጅ እጥረት እየተከሰተ ያለው የባጃጅና የሞተር አሽከርካሪዎች እየፈጠሩት ባለው ስወራ ነው" ብለዋል።

የባጃጅና የሞተር አሽከርካሪዎች ቢንዚን በሚገባበት ወቅት በታንከር የሚቀዱትን ነዳጅ ወደ ሌላ እቃ በመገልበጥ በቀን እስከ 10 ጊዜ እየቀዱ ስለሚሰወሩ ለእጥረቱ መከሰት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አኬሎ ኡቦንግ ስለጉዳዩ ተጠይቀው "የቤንዚን እጥረት እየተከሰተ ያለው አንዳንድ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ከማደያዎች ጋር በመመሳጠር ነዳጅ በሌሊት እየቀዱ ወደ ጎረቤት ሀገር ስለሚወስዱ ነው" ብለዋል።

ከሁለት ቀን በፊት በተደረገ ክትትል 26 በርሜል ቤንዚንና ናፍጣ ወደ ጠረፍ አካባቢ ለመውሰድ ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል።

ቢሮው ችግሩን ለመከላከል ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንና በጥቁር ገበያ የሚሸጠውን ነዳጅም ሆነ ወደ ሌሎች አካባቢ የሚወሰደውን ነዳጅ ለማስቆም ሕዝቡ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ላይ ኢትዮጵያ የምታስገባውን ነዳጅ በሕገ ወጥ መልኩ ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚወጣ መግለጻቸው ይታወሳል።

የየአካባቢው አስተዳደር አካላትም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚጓጓዘውን ነዳጅ ከነተሽከርካሪው እንዲወርሱ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም