ዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ ለምታከናውናቸው ተግባራት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

202

የካቲት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ ለምታከናውናቸው ተግባራት የሚያደርገውን የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንገድ አስተዳደር ጋር በመተባበር በስራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።

አውደ ጥናቱ በዋናነት በኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በማሽነሪ ከሚሰሩ ስራዎች በተጓዳኝ በቴክኖሎጂን በመታገዝ በሰው ኃይል ሊከናወኑ የሚችሉ ተግባራትን ለማመላከት ያለመ ነው፡፡

በዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ዳይሬክተር አሌክሶ ሙሲንዶ እንዳሉት፤ የዓለም የስራ ድርጅት ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ ለምታከናውነው ተግባር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

አውደ ጥናቱም ጥራቱን የጠበቀ መንገድ በመገንባት የስራ እድል መፍጠር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር ለማድረግ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና በመስጠት በርካታ የስራ እድል መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመው፤ ድርጅታቸው ለዚሁ ስራ ቴክኒካል ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንገድ አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር የትምጌታ አስራት በበኩላቸው በፌዴራል መንግስት በተያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ብቻ በየዓመቱ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።

አውደ ጥናቱ በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ልምድ ለመውሰድ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ ተቋሙ ባለው የስልጠና ማዕከል አማካኝነት ከዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት ጋር በመተባበር  በቀጣይ በጋራ ሊሰሩባቸው በሚችሉ መርሃ-ግብሮች ላይም ምክክር ይደረጋል ነው ያሉት።

በዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት የማህበረሰብ ስራ የፖሊሲ አማካሪው አስፋው ኪዳኑ፤ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር ከሚቻልባቸው ዘርፎች አንዱ የመንገድ ግንባታ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እድገትና ብልጽግናን ለማምጣት በሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ማሽን ከሚከናወኑ ስራዎች በተጨማሪ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠትና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚቻል አመላክተዋል።

ስልጠና በመስጠት በተለያዩ ክልሎች በሚገነቡ የጠጠርና አስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ሰፊ የሰው ኃይል ማሰማራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼