በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ500 ሊትር በላይ ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋለ

60

ሆሳዕና፤ የካቲት 29/2014 (ኢዜአ) በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ500 ሊትር በላይ ቤንዚን በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቀ።

ቤንዚኑን መቆጣጠር  የተቻለው ዛሬ የሰሌዳ ቁጥር  በሌለው የባጃጅ  ታክሲ በጀሪካን ተጭኖ ከወራቤ ከተማ ወደ ቡታጅራ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ከህዝብ ጥቆማ የደረሰው በከተማዋ የተቋቋመው ህገ ወጥ ንግድ መከላከል ግብረ ሃይል ባደረገው ክትትል   ቡታጅራ መውጫ  ላይ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሻፊ ሙዜ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ግብረ ሃይሉ የባጃጁ አሽከርካሪውን ከሌላ ተጠርጣሪ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ በምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማው የተለያዩ ምርቶችን እየሸሸጉ  የምርት እጥረት እንደተከሰተ በማስመሰል የዋጋ ጭምሪ በማድረግ የሚሰሩ ነጋዴዎችን  ለመቆጣጠርና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ  ግብረ ኃይሉ ጥብቅ  ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የከተማው ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ ያለ በቂ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህዝብን በማስመረር  ለግል ጥቅማቸው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ፀጥታው መዋቅር የተሰጠውን ተግባር በመወጣት ላይ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ የትራፊክ ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ የባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ ባጃጅ ጭኖ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ቤንዚን ነዳጅ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን አጠናክሮ በማስቀጠል ፍትሐዊ የንግድ ስርዓት ለማኖር  የተጀመረው ጥረት  ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም