ለአቅመ ደካማ እናቶችና ህጻናት 700 ሺህ ብር ግምት ያለው ድጋፍ ተደረገ

69

አምቦ የካቲት 29/2014 (ኢዜአ) በምእራብ ሸዋ ዞን ሴት የመንግስት ሰራተኞች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ እናቶችና ህጻናት 700 ሺህ ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ፡፡

የምእራብ ሸዋ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ተወካይ ወይዘሮ አስካለ ቀነአ በወቅቱ  እንዳሉት ድጋፉ በዞኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በሴት ሰራተኞች የተሰበሰበ ነው።

ድጋፉ የምግብ እህልና አልባሳትን ያካተተ መሆኑን ጠቁመው  ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ በአምቦ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና ደጋፊ ለሌላቸው ህጻናት የሚውል መሆኑን አመልክተዋል።

"ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ሴቶች በማህበረሰቡ ውሰጥ ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኙ መሰረት የጣለ በመሆኑ በየዓመቱ እናከብረዋለን" ብለዋል፡፡

የዓለማችን ሴቶች ባደረጉት ተጋድሎ በሴቶች ላይ ይደርሱ የነበሩ ጫናዎች እየቀነሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ሴቶች ለጠላት የማንበረከክ ፤  እጃችንን ለችግር የማንሰጥና በአገራችን ጉዳይ የማንደራደር በመሆናችን እንኮራለን " ሲሉ አክለዋል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን ሴቶች ሊግ ሃላፊ ወይዘሮ አያንቱ ይሻው በበኩላቸው "ሴቶችን መደገፍ ሁሉንም ማህበረሰብ መደገፍ ስለሆነ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል፡፡

 "የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ስናከብር ያገኘነውን ድል ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ቃል በመግባት ነው" ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች  በጋራ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም