ጣና ፍሎራ ወደ ውጭ ገበያ ከላከው የአበባ ምርት 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮና ዶላር ገቢ አስገኘ

141

ባህር ዳር ፤ የካቲት 29/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የሚገኘው ጣና ፍሎራ ማህበር ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት ገበያ ከላከው የአበባ ምርት 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮና ዶላር ማስገኘቱን አስታወቀ።

የማህበሩ  የገበያ ልማት ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  ማህበሩ የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ያስገኘው  በ40 ሄክታር መሬት ላይ እያለማ ካለው  የአበባ ምርት  ሽያጭ ነው።

ማህበሩ ለውጭ ገበያ አምርቶ የሚያቀርባቸው ቀይ፣ ነጭ፣ ቢጫና ሮዝ ቀለሞች ያላቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በዚህም  ማህበሩ ያስገኘው ገቢ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2021 ውስጥ  37 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአበባ ዘንጎችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ እንደሆነ አመልክተው፤ የዕቅዱንም  86 በመቶ ማሳካቱን ተናግረዋል።

ከምርቱም ሽያጭ  ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ሆላንድ ከተላከው የአበባ ምርት 4 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ከተላከው ደግሞ  1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

የተገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም በምርት 20 በመቶ፣በገቢ ደግሞ የስምንት በመቶ ጭማሪ እንዳለው ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተበት ወቅት በመሆኑ በምርት ሽያጭ ላይ ችግሮች አጋጥሟቸው እንደነበር አውስተዋል።

አቶ አብነት እንዳሉት፤  የአበባ ልማቱ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ባለፈ ከ800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ማህበሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

በማህበሩ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት አንደበት አስማረ በሰጠው አስተያየት፤በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ጠንክሮ በመሥራት ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል።

ሰራተኞቹ በሚያስመዘግቡት የስራ ውጤት  መሰረት ማህበሩ  በሚያደርገው የክፍያ ጭማሪ ተጠቃሚነታቸው ከፍ እያለ መምጣቱን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ሸጋናት አቤ ናት።

በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አጠቃላይ የኤክስፖርት ዘርፍ  አስተባባሪ አቶ አንተነህ ዓለሙ በበኩላቸው፤ የአበባ ምርት በሀገር አቀፍ ደረጃ  ከቡናና ጫት በመቀጠል የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘ ነው ብለዋል።

በክልሉ አበባ ልማት ላይ በስፋት መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን የሚቻልበት እድል ሰፊ መሆኑን ጣና ፍሎራን  በማሳያነት በመጥቀስ  ገልጸዋል።

ጣና ፍሎራ ወደ አበባ ልማት ከገባ ከ10 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረና ከአበባ በተጓዳኝም በአቮካዶ ልማት እየተሳተፈ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም