በፌዴራሊዝምና በሕገ መንግስት አስተምህሮ ጋዜጠኞች ግንዛቤያቸውን በማጎልበት አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ማገዝ አለባቸው

185

አዲስ አበባ የካቲት 29/2014(ኢዜአ) የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በፌዴራሊዝምና በሕገ መንግስት አስተምህሮ ግንዛቤያቸውን ይበልጥ በማጎልበት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ መሳካት አጋዥ እንዲሆኑ የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ገለጸ፡፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ቁልፍ አገራዊ ጉዳዮችን በጥናት በመለየት የምክክር ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ እንደሚሰራም ተመላክቷል።

የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በአዋጅ ቁጥር 1123/2011 ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሆን ተደርጎ የተዋቀረ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡

ዓላማውም ዜጎች በአገራቸው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በህገ መንግስት አስተምህሮ በፌደራሊዝም ስርዓቱ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው፡፡

የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለየሱስ ታዬ፤ በኢትዮጵያ የፌደራሊዝምና ህገ መንግስት ትምህርት የሚሰጥባቸው ተቋማት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በህገ መንግስታዊ አስተምህሮና ፌደራሊዝም ስርዓት ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ በመያዝ በኩል ውስንነት ይታይባቸዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ማዕከሉ ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ የተሻለ መረዳት እንዲኖረው የሲቪክ ማህበራትን፣ ተማሪዎችንና የተለያዩ አደረጃጀቶችን ለማሰልጠን በያዘው ዕቅድ መሰረት ለጋዜጠኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት ስራውን መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ለመወያየትና ህብረተሰቡን ለማስተማር ሳይንሱን በሚገባ መረዳት አለባቸው ብለዋል፡፡

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በዜጎች የጋራ ጉዳይ ላይ “ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር” የጀመረውን ስራ ለመደገፍ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ባለሙያዎች በህገ-መንግስታዊ አስተምሮዎችና ፌደራሊዝም ላይ የተሻለ ሳይንሳዊ እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

የህገ መንግስት አስተምህሮዎችንና የፌደራሊዝምን ጽንሰ ሀሳብ በዜጎች ላይ ለማስረጽ የመገናኛ ብዙኃንና የሚመለከታቸው ተቋማት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ማገዝ አለባቸው፡፡

ለምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ ስራ በሁሉም ዘንድ ድጋፍ እና እገዛ ሊደረግለት እንደሚገባና ለውይይት የሚቀርቡ ጉዳዮች በአግባቡ ተጠንተው የተለዩ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

በማህበረሰቡ፣ በምሁራን፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሲቪክ ማህበራት አማካኝነት ጉዳዮችን በአግባቡ የመለየት ስራም ይጠበቃል ነው ያሉት።

ዜጎች ከመወያየታቸው በፊት ስለሚወያዩበት ጉዳይ በቂ መረዳት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የግጭት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት መለየት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

“በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በፖሊሲ ጉዳይ ላይ ውይይት አይደረግም፤ ምክንያቱም የፓርቲ ጉዳይ ነው” የሚሉት ዶክተር ኃይለየሱስ፤ የውይይት ጉዳዮችን በጥንቃቄ መምረጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በፌደራሊዝምና ህግ መንግስታዊ አስተምህሮዎች ዙሪያ ለጋዜጠኞች የሚሰጠው ስልጠና ሁለተኛ ዙር ላይ ደርሷል፡፡