ሴቶች እድሉን ካገኙ በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ይችላሉ

87

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29/2014(ኢዜአ) ሴቶች እድሉን ካገኙ በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ይችላሉ ሲሉ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሴት የህክምና ባለሙያዎች ገለፁ፡፡

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ 111ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ 46 ጊዜ ''እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ይገኛል።

እለቱን አስመልክቶ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በሴት የህክምና ባለሙያዎች ብቻ የተመራ ቡድን የተለያዩ የቀዶ ህክምና አገልግሎቶችን ሰጥቷል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሜዲካል አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሊዲያ ተፈራ በዚሁ ወቅት ሴቶች እድሉን ካገኙ በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ይችላሉ ብለዋል።

ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በሆስፒታሉ በሴቶች ብቻ የተመራ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሴቶች በህክምናውም ዘርፍ ያላቸውን ብቃት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሆስፒታሉ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሴት ነርሶች ያሉ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ሊዲያ፤ ከዚህም በተጨማሪ 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች በሆስፒታሉ የሰመመን ህክምና ባለሙያዎች (አንስቴቲስት) ናቸው ብለዋል።

የህክምና ቡድኑ ከሁለት ወር ህጻናት ጀምሮ ለአዋቂዎች ጭምር ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል።

የሰመመን ህክምና ባለሙያ የሆኑት ናርዶስ በለጠ፤ የህክምና ቡድኑ በዛሬው እለት እየሰጠው ያለው አገልግሎት ሴቶች በየትኛውም ሙያ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ሆስፒታሉ የጠቅላላ ቀዶ ጥገና፣ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ሰብ ስፔሻሊስቲ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ማርታ ፍቅረ ማሪያም በበኩላቸው፤ በዛሬው እለት በሴቶች ብቻ የተመራው የቀዶ ህክምና አገልግሎት የጤና ባለሙያ መሆን ለሚፈልጉ ለታዳጊ ሴቶች አርአያ ለመሆን  ጭምር ታስቦ እየተከናወነ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም