ጃፓን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ግቡን እንዲመታ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች

75

የካቲት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የታለመለትን ግብ እንዲመታ ጃፓን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።

አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ጃፓን በአድናቆት ትመለከተዋለች ብለዋል።

አገራቸው በታሪኳ የገጠማትን ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች በተለያዩ ምክክሮች ማለፏን ጠቁመው ይህም ጃፓን ከሠላሟ አልፎ አሁን ለደረሰችበት የኢኮኖሚ ቁንጮነቷ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።  

አገራቸው ጃፓን ከበርካታ ዓመታት በፊት በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት በማኅበረሰቦች መካከል ትልቅ ቁርሾ መፍጠሩን ጠቁመው ያንን አስከፊ ታሪክ በእርቅ መደምደማቸውን አስረድተዋል።  

በእርስ በርስ ጦርነቱ በርካታ ሰዎች ቢሞቱም፤ ተጎጂዎች ቢኖሩም በእርቅና በመቻቻል ጃፓን ያንን ሁሉ አልፋ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሯን የአገራቸውን ታሪክ ለተሞክሮ አንስተው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያም የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ህዝብ በርካታ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ጠቁመው በሂደቱ ሁሉም ሊሳተፉ እንደሚገባ  ገልጸዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አገራዊ ምክክሩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረው አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ጃፓን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ነው አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ያረጋገጡት።   

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ አገራዊ ምክክር ማካሄድ ፍላጎት እንዳለው አምናለሁ ያሉት አምባሳደሯ በምክክር ሂደቱ ጃፓን ድጋፍ ማድረግ በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ ግን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ ነች ብለዋል።

በሌላ በኩል ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የጃፓን ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ በስፋት እንዲመጡ ጄትሮ (JETRO) በተሰኘው የጃፓን የውጭና የገቢ ንግድ ተቋም በኩል በኢትዮጵያ ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

በሌላ በኩል በዘላቂ ልማት ግቦች፣ በተለይም ደግሞ በግብርና ልማት በኃይል አቅርቦት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

ጃፓን ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የሰው ኃብት ልማት ግንባታ ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ በመልሶ ማቋቋም ሥራም ተሳትፎዋን ትቀጥላለች ብለዋል።  

ዘንድሮ 50ኛ ዓመቱን የሚይዘው የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (JICA) ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በውይይት የሚወሰን መሆኑን ገልጸዋል።

የጃፓንና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1930 ነበር።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም