ሚኒስቴሩ በክልሉ ያለውን ቡናና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ተጠብቆ እንዲለማ በትብብር እንደሚሰራ አስታወቀ

89

ሚዛን፣ የካቲት 28/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን ቡናና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ተጠብቆ እንዲለማ በትብብር እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከሚኒስቴሩና ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተውጣጣ ግብረ ሃይል በክልሉ  ቤንች ሸኮ ዞን እየተካሄደ ያለውን ያረጀ ቡና ጉንደላ እንቅስቃሴ በመስክ ተመልክቷል።

በመስክ ምልከታው ወቅት  በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ግብይት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ እንዳሉት፤ ቡናን የሚያመርቱ አካባቢዎች የቡና ስምና የማሳ ስፋት ብቻ ይዘው እንዳይቀሩ ምርታማነትና ጥራት እንዲጠበቅ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።

ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር ባለፈ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚያበረክተው አስተዋዕኦ ከፍተኛ በመሆኑ ምርታማነቱን ለማሳደግ በመንግሥት የተዘረጉ  የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ሊተገበሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘርፉ ከንግግር ያለፈ ተግባርን የሚሻ በመሆኑ በክልሉ ያለውን ቡናና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ሌላውንም እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ተጠብቆ እንዲለማ ሚኒስቴሩ በትብብር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ እና አመራር አካላት በባለቤትነት መንፈስ በመንቀሳቀስ ለአርሶ አደሩ በቅርበት አሰፈላጊውን  ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ  ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤ "አርሶ አደሩ በሚያመርተው የቡና ማሳ ልክ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ የቡናን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በመስክ እንደተመለከቱት በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን  የቡና ምርትና ጥራትን ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ተግባር የሚያበረታታ መሆኑንም አውስተዋል።

"ክልሉ አዲስ ቢሆንም የቡናና ቅመማ ቅመም ማዕከል በመሆኑ  አስፈላጊውን ደጋፍ በማድረግ ሀብቱ ወደ ኢኮኖሚ ተቀይሮ ለአርሶ አደሩ ብሎም ለሀገራችን ከፍ ያለ ኢኮኖሚ እንዲያስገኝ እንሰራል ብለዋል ዶክተር አዱኛ ።

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ጥራቱን ለማሻሻል ከሚያግዙ መንገዶች አንዱ የሆነውን ያረጀ ቡና ጎንደላ በተሻለ ሁኔታ መፈጻም እንዳለበት አመልክተዋል።

በክልሉ 541 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ልማት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ አሥራት መኩሪያ ናቸው።

ሆኖም በቡና ከተሸፈነው ውስጥ 100 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በእርጅና ምክንያት ምርት የመስጠት አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል  ዘንድሮ 5 ሺህ 340 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ያረጀ ቡና ነቀላና ጉንደላ ለማካሄድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ እስካሁንም 3 ሺ 73 ሄክታር ላይ መከናወኑን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሮች ከቡና ልማት የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዲሆኑ  የቡና  የማደስ ተግባሩ በየደረጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ የቂጤ ቀበሌ አርሶ አደር ንጉሴ እሼቱ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ 7 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ቡና እያለሙ መሆኑን ገልጸው ምርታማነትን ለማሻሻል ሶስት ሄክታር ላይ የሚገኘውን በመጎንደል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም  እየተንከባከብኩ ነኝ ብለዋል።

ቀደም ሲል ካላቸው የቡና  መሬት እስከ   120 ኩንታል  ስፔሻሊቲ  (ልዩ)  ቡና ያገኙ  እንደነበር ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ግን ያረጀ ቡና ባሳደረባቸው ተጽዕኖ 55 ኩንታል ብቻ  ለገበያ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም