በኢንዱስትሪ ልማት ላይ የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የኢትዮጵያን ልማት ሊደግፍ ይገባል

70

የካቲት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢንዱስትሪ ልማት ላይ በተለይም የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የኢትዮጵያን ልማት መደገፍ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታን መርቀው በከፈቱበት መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት የኢንዱስትሪ ዘርፍ በመንግስት ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ልማት ላይ በተለይም የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የኢትዮጵያን ልማት መደገፍ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

በተለይ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ተፈላጊነት ቀጣይነት ያለው በመሆኑ የግሉ ዘርፍ በስፋት ሊሰማራበት ይገባል ብለዋል።

መንግስት ዘርፉን ለመደገፍ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠው፤ ኢትዮጵያዊያን በመደጋገፍ ለአገር ልማት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ መንግስት አገር በቀል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የብረታ ብረት ልማት ለምጣኔ ሃብት ሽግግር ሞተር ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቅሰው፤ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረትና ለስራ እድል ፈጠራ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ500 በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ የብረታ ብረት ፋብሪካዎች መኖራቸውንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማስፋፋት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ያሉ ፕሮጀክቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ የተከፈተው የአዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ ቀደም ሲል ሲያመርታቸው ከነበሩ ሚስማርና ቆርቆሮዎች በተጨማሪ ፌሮዎች፣ የተለያዩ ሽቦዎች እና ሌሎች የብረታ ብረት ውጤቶችን ያመርታል።

በአሁኑ ወቅት የፋብሪካው ካፒታል 7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን በ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ አድርጎ ተጨማሪ የብረታ ብረትና ቱቦላሬ ምርቶችን ማምረት ጀምሯል።

ፋብሪካው በአሁኑ ጊዜ ለ900 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ደግሞ ለ3 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም