በገበያ መር ክላስተር ግብርና አርሶአደሮች ከዕለታዊ ፍጆታ ባለፈ እስከ 50 በመቶ ምርታቸውን ለገበያ አቅርበዋል

የካቲት 27/2014/ኢዜአ/ ባለፉት ሁለት አመታት በገበያ መር የክላስተር ግብርና የተሳተፉ አርሶአደሮች ከዕለታዊ ፍጆታ ባለፈ ከሃያ እስከ ሀምሳ በመቶ ምርታቸውን ለገበያ ማቅረባቸውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ገለጸ።

በኤጀንሲው የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ተጫነ አዱኛ  አርሶአደሮች ከግለሰብ ፍጆታ ባለፈ ገበያ መር የሆነ ምርት እንዲያቀርቡ የሚያስችል ፕሮጀክት ተነድፎ ምርቶችን በመምረጥና አካባቢዎችን በማደራጀት ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ እ.አ.አ ከ2019 እስከ 2024 የሚቆይ መሆኑንና የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ወይንም ገበያ መር የክላስተር ግብርና እንደሚባል የገለጹት ሃላፊው በኢትዮጵያ የተለያዮ አካባቢዎች እየተተገበረ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።

በገበያው ተፈላጊ የሆኑ እንደ ስንዴ፣ በቆሎ፣ የቢራ ገብስ ፣ ሰሊጥ፣ ጤፍ ፣ አቦካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም ምርቶችን በተለያዮ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ 300 ወረዳዎችና በአርሶአደር የክላስተር ቡድኖች አማካኝነት ወደ ህብረተሰቡ ቀርበዋል ብለዋል።

በተዋቀሩት የክላስተር ቡድኖች 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል ያሉት ሃላፊው ከነዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን አርሶአደሮች በምርት ክላስተር ቡድን ራሳቸውን በማደራጀት በየዓመቱ ከሚሰበስበው የግብርና ምርት በተሻለና ከእለታዊ ፍጆታ ባለፈ ከ20 እስከ 50 በመቶ ምርት ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የግብአት አቅርቦት፣ የምርት ስራ፣ ክምችትና የገበያ ሰንሰለትን ማቀፉን ጠቁመው አርሶአደሮች ምርት የት እሻጣለሁ አንዳይሉ ከገዢው ጋር በኮንትራት ስምምነት የግብይት ትስስር የሚፈጥሩበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች በከብትና ዶሮ እርባታ፣ በአሳና ወተት ምርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ገበያ መር የክላስተር ግብርና ስራዎች እንደሚከናወኑ ነው አቶ ተጫነ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም