በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የውሃ ተቋማትን ለማቋቋም 16 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

61


ባህር ዳር ፤የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ቡድን ዝርፊያና ውድመት የደረሰባቸው የውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማቋቋም የሚያግዝ 16 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በውሃ መሰረተ ልማቶች፣ በዞንና ወረዳ ውሃና ኢነርጂ መምሪያዎችና ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈፀሙ ተወስቷል።
ተከትሎም በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፋ መጠጥ ውሃ ችግር መጋለጣቸውን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አደም ወርቁ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት መልሶ በማቋቋም የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል በምዕራብ አማራ ዘጠኝ ከተሞች ከሚገኙ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች ጋር በመተባበር 16 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ከድጋፉ ውስጥ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ለኮምቦልቻ እና ለከሚሴ ከተሞች የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች የተሰጠው ይገኝበታል።
በርካታ ዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ ካርቶን ወረቀት እንዲሁም ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ የቧንቧ መለዋወጫዎች እና መሰል ቁሶች ሌላው ድጋፍ መሆኑን አመላክተዋል።
በቢሮው አስተባባሪነት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ለአራት የዞን እና ለ45 የወረዳ ውሃና ኢነርጂ መምሪያዎችና ውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች ለሥራ ማስጀመሪያ እንዲሆን የተለያዩ የቢሮ ቁሶች መለገሱንም ጠቅሰዋል።
“በቀጣይም በከተሞች ለከተሞች ትብብር የቁሳቁስ ድጋፉ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል አቶ አደም።
በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የውሃ ተቋማትን ወደነበሩበት በመመለስ የተሟላ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ለመስጠት አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ከክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም