ኢቢሲ ተደማጭ፣ ተደራሽና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ሆኖ ለመውጣት እየሰራ ነው

174

ባህር ዳር፤ የካቲት 26/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ተደማጭ፣ ተደራሽና በቀጠናው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ሆኖ ለመውጣት እየሰራ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ አስታወቁ።

ኢቢሲ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ያስገነባቸውን የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስቱዲዮችን ዛሬ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለና ሌሎች የፌዴራልና ክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት አስመርቋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ፍስሃ ይታገሱ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ኢቢሲ አንጋፋነቱንና ተወዳዳሪነቱን ይዞ ለመዝለቅ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንዲስፋፉ፣ የመረጃ ነፃነት ተደራሽ እንዲሆንና የኢትዮጵያ ህዝብ መረጃ የማግኘት መብቱ እንዲረጋገጥ የረጅም ጊዜ ልምዱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ኢቢሲ ተደማጭ፣ ተደራሽና በአካባቢው፣ በኢትዮጵያና በቀጠናው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ሆኖ ለመውጣት እየሰራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስረድተዋል።

አቶ ፍስሃ እንዳሉት በሪፎርሙ የሰው ኃይሉን በማብቃት፣ በማሰልጠንና ሥርዓት በመዘርጋት አሰራሩን ለማዘመንና በየክልሉ ስቱዲዮዎችን በመገንባት ተደራሽ ለመሆን እየሰራ ይገኛል።

''የቴሌዥንና የሬዲዮ ስቱዲዮዎችን ወቅቱን በዋጀ ቴክኖሎጂ መገንባት ይበልጥ ወደ ህዝብ እንድንቀርብ ያደርገናል፣ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነን እንድንዘልቅም ያግዘናል'' ብለዋል።

ኢቢሲ በስራዎቹ መንግሥትና ህዝብን ይበልጥ ለማቀራረብ በቀጣይ በሐረር፣ በመቱና በሀዋሳ ከተሞች ተመሳሳይ ስቱዲዮዎችን እየገነባ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፣ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አሁን አድማሱን በማስፋት በባህር ዳር ራሱን የቻለ የማሰራጫ ስቱዲዮ በመክፈቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ዛሬ የምንመርቀው አዲሱ ስቱዲዮም በክልሉ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር አንድ አማራጭ ሆኖ ህዝባችን በመረጃ የበለፀገ እንዲሆን በማድረግ በኩል የላቀ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

"በመሆኑም የህዝቡን የፖለቲካ ንቃት፣ ማህበራዊ ህይወቱንና የኢኮኖሚ አድማሱን ለማሳደግ መረጃ ትልቅ ሃብት ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ይህም መንግሥት የሚሰራቸውን ስራዎች በቀላሉ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ያስችላል።

የክልሉ መንግሥትም መረጃ በመስጠት ከድርጅቱ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፣ ህዝቡ በየአካባቢው ሃሳቡን የሚገልጽባቸው፣ የሚወያይባቸውና የሃሳብ ብዝሃነት የሚንፀባረቅባቸው ስቱዲዮዎችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዛሬ በባህር ዳር አስገንብቶ ያስመረቃቸው የሬዲዮና ቴሌቪዥን ስቱዲዮዎችም ይህንን የሚያግዙ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይ በአካባቢው የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነገ የተሻለ ጋዜጠኞች ሆነው እንዲወጡ ልምምድ የሚያደርጉበትና ብቃታቸውን የሚያሳድጉበት እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም