ኢዜአ የኢትዮጵያን ህልውና በማስቀጠል የቁርጥ ቀን ተቋም መሆኑን በተግባር አሳይቷል

80

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ህልውና በማስቀጠል የቁርጥ ቀን ተቋም መሆኑን በተግባር አሳይቷል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን የ80 ዓመታት ጉዞ የሚዳስስ አውደ-ርዕይ ተከፍቶ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።

"በአገራዊ ህልውና ማስከበር ዘመቻ ወቅት የኢዜአ ሚና እና የዜና አገልግሎት አመጣጥና የኢዜአ ታሪካዊ ጉዞ" በሚል ሁለት የመወያያ መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ አሸባሪው ህወሓት  ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት ተገዶ ወደ ጦርነት ከገባ ጀምሮ ባለፉት ወራት ኢዜአ በግንባር ያከናወናቸውን ተግባራት አድንቀዋል።

በዚህም አሸባሪው ህወሓትና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የነበራቸውን ሴራ በማክሸፍ ኢዜአ ትልቅ አበርክቶ እንደነበረው አንስተዋል።

መንግሥትና ኢትዮጵያውያን ለአሸባሪው ቡድን ያሳዩትን የሰላም በር በስፋት በመዘገብ ኢዜአ የኢትዮጵያን የሰላም እጆች ለዓለም ከፍ አድርጎ አሳይቷልም ብለዋል።

የኢትዮጵያን የእውነት ድምጾች በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ በማሰማት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ተቋም መሆኑን ኢዜአ በተግባር ማሳየቱንም ዶክተር ቢቂላ አስረድተዋል።

ኢዜአ ኢትዮጵያውያን በህብረ ብሔራዊ አንድነት ለአገራቸው ህልውና እንዲታገሉ አጀንዳ መፍጠር የቻለ የዜና አውታር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለያዩ የጦር ግንባሮች በመገኘትም ትኩስ፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን በማድረስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ የውጭ ኃይሎችና ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በከፈቱበት ወቅት ኢዜአ በትክክለኛ መረጃ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱን መመከቱንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አርበኝነት ዳግም በተቀጣጠለበት ወቅት የማይቀረው ድል እንዲመጣ የኢዜአ ሚና የላቀ መሆኑንም በጽሑፋቸው አብራርተዋል።

በድህረ ድል የኢትዮጵያ የሰላምና የልማት አጀንዳዎች ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አጠናክሮ መቀጠሉንም ነው የተናገሩት፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር  ዮሐንስ ሽፈራው ኢዜአ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ከተለያዩ አካባቢዎች መረጃን በቀላሉ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ኢዜአ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመታደግ ሂደት ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፉን ገልጸው፤ በቀጣይም በሀገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች ተደራሽነቱን አስፍቶ መቀጠል እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

ለዚህ ደግሞ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኢዜአ  በ1934 ዓ.ም ጀምሮ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም