የሚዲያ ተቋማትን በማጠናከር ለአገር ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ መስራት ይገባል

56

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሚዲያ ተቋማትን በማጠናከር ለአገር ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ መስራት እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ የ80 ዓመት መስረታን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት  አውደ ርእይና የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ኢዜአ  በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም መሆኑን አስታውሰዋል።

ኢዜአ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ የተመሰረተና ረጅም እድሜ አላቸው ከሚባሉ የሶስተኛው ትውልድ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት እንደ አገር የኢትዮጵያን ረጅም ታሪክ የሚሸከሙ አገርን የሚያሻግሩ ተቋማትን የማፍረስ ልማድ እንደሚስተዋልም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ ኢዜአ በተለያዩ ጊዜያት ተቋማዊ መዋቅሩን በማሳነስ ሚናውን ለሌሎች ተቋማት ከመስጠት እስከ መፍረስ ስጋት የደረሱ ሂደቶችን እንዳለፈ  አስታውሰዋል።

አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ በመገንባት ለትውልድ ለማሻገር የተቋማት ግንባታ ወሳኝ ሚና  እንዳለው ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የሚዲያ ተቋማትን በማጠናከር ለአገር ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አክለውም እንደ አገር ብሔራዊ የታሪክ ማስታወሻን ሊያስቀምጡ የሚችሉ ተቋማትን ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢዜአን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ያሉባቸውን ችግሮች እየቀረፉ በማስተካከልና በማጠናከር የዘመኑን ትውልድ ጥያቄ እንዲመልሱና አገር ለመገንባት እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

አገር የመውደድ አንዱ መለኪያ ተቋማትን ማጠናከር መሆኑን በመግለጽ፡፡

ኢዜአ የመረጃ ጥራትና ተደራሽነትን ለማጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለበትም ነው የጠቆሙት፡፡

የአገሪቱ ተቋማትም ከኢዜአ ጋር ተባብረው በመስራት መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በዚህም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በመላው አፍሪካ ተፅዕኖ እንድትፈጥር የኢትዮጵያ ጉዳዮችም የአፍሪካ ጉዳዮች ሆነው የሚደመጡበትን እድል መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል።

አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን  ተቋማትን የማጠናከር ተልዕኮ ይዘው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም