የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶች በመስጠት ተጠናቀቀ

190

ድሬዳዋ፤ የካቲት 25/2014(ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሹመቶች በመስጠት መደበኛ ጉባኤውን አጠናቀቀ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት የመንግስት ሥራ አስፈጻሚውና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን የግማሽ በጀት ዓመቱን  ከገመገመ በኋላ የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠት ነው ጉባኤውን ማምሻውን ያጠናቀቀው፡፡

ጉባኤው የተጓደሉ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በሙሉ  ድምፅ የሾመ ሲሆን በዚህም ወይዘሮ ኢንቲሳር አብዱረህማን የሴቶች፣ የህጻናትና ወጣቶች ቋሚ ኮሚቴ እና   አቶ አህመድ ሰኢድ ደግሞ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አድርጓል፡፡

እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቅራቢነት አቶ ብሩክ ፈለቀን የድሬዳዋ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ፣  ወይዘሮ ጫልቱ ሁሴንን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ሃየር ሀጂ ኑርን ደግሞ የፕብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አድርጎ የምክር ቤቱ ጉባኤ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

በተጨማሪም አቶ ሱሌይማን አሊ የድሬዳዋ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ፣ ወይዘሮ ፋኪያ መሐመድ የድሬዳዋ አስተዳደር ዋና ኦዲተር  ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እንዲሰሩ በሙሉ ድምጽ ሾሟቸዋል፡፡

የምክር ቤቱ ጉባኤ  አቶ አብዲ አደንን  የድሬዳዋ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኛ እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡

ተሿሚዎቹ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ  የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈቲሂያ አደን ፤የአስተዳደሩ አስፈጻሚ አካል በቀጣዩ ወራት የከተማውን የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነት ችግሮችን ለማቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅቶ  ስራውን አጠናክሮ  እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የአስተዳደሩን የሥራ አጥ ቁጥር የመቀነስ፣ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ፣ የህዝብ የመልካም አስተዳደርና የገጠሩን ህብረተሰብ አንገብጋቢ የልማት ጥያቄዎች መመለስ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡