በደቡብ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ማሰባሰብ ተጀመረ

106

ሀዋሳ የካቲት 25/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል የ2014 ክልላዊ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምርት ማሰባሰብ ስነ ስርአት በወላይታ ዞን ተጀመረ።

መርሃ ግብሩን በወላይታ ዞን ሁምቦ ወረዳ አምፖ ኮይሻ ቀበሌ በመገኘት ያስጀመሩት በምክትል ርእስ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች ናቸው።

በወላይታ ዞን የሁምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃገና አይዛ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት በወረዳው በበጋ መስኖ ልማት 136 ሄክታር መሬት መልማቱን ገልፀዋል።

በሶስት ክላስተር በዘመናዊ መስኖ አውታሮች በተካሄደው የመስኖ ልማት ከወረዳው የተመረጡ 310 አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በወረዳው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካሄደ መስኖ ልማት 5 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ እስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በቀበሌው በኩታ ገጠም ማሳ የለማ የስንዴ ምርት በኮምባይነር እየተሰበሰበ ሲሆን በምርት ማሰባሰቡ ስነ ስርአት ላይ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የቀበሌው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም