ኢዜአ በአዲስ ምዕራፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል

98

የካቲት 25/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየታገዘ በአዲስ ምዕራፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ሲሉ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ተናገሩ።

የኢዜአ 80ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ሲሆን በዛሬው እለትም ዓውደ ርእይ ተከፍቷል ፣ የፓናል ውይይትም ይካሄዳል።

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፤ በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ተቋሙ በ80 ዓመታት ጉዞው ያከናወናቸውን በርካታ ውጤታማ ተግባራትና የገጠሙትን ፈተናዎች አብራርተዋል።

ኢዜአ እነዚህን ዓመታት አልፎ ዛሬ ላይ እንዲዘክር በየዘመኑ የነበሩ የተቋሙ አመራርና ሙያተኞቹ ሚና የላቀ መሆኑን አስታውስዋል።

ኢዜአ ከመፍረስ አደጋ ወጥቶ ራሱን ችሎ በአዋጅ ቁጥር 1115/2011 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ሆኖ ለህዝብና ለሀገር የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢዜአ መልሶ እንዲያንሰራራ እድል በመስጠታቸው አገር የገጠሟትን ትላልቅ ፈተናዎች በመመከት ሂደት ግንባር ድረስ ዘልቆ ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ ሲያደርስ መቆየቱን አብራርተዋል።

“ዴሞክራሲና የሃሳብ ነፃነት ከዜጎች የእለት ተለት ህይወት ሙላት ተነጥሎ አይታይም፤ መረጃ ለሀገራዊ ልዕልና ወሳኝ ነው” ብሎ በመንግስት በመታመኑ ለኢዜአ እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ወደ አዲስ ምዕራፍና ሽግግር የሚዘልቅበት አጓጊ ጊዜ ላይ እንዲደርስ አስችሎታል ብለዋል።

ኢዜአ በአዲስ አበባ ያለውን ማዕከል ጨምሮ በ38 ቅርንጫፎቹ ህብረብሄራዊ ገፅታ እንዲጠናከርና በግብዓት እንዲሟሉ ለማድረግም የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአን በውጭ ቋንቋዎች በአፍሪካ ቀዳሚ ማድረግ ወደሚያስችሉና በዜና አገልግሎት ዘርፍ የአገራችንን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደሚያረጋግጡ መዳረሻዎች መውሰድ የሚያስችል የጥናት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተያዘው ዓመትም ተቋሙ ባስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ውስጥ ከሚገኙ ሶስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ስቱዲዮዎች ሁለት የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎችን በማሟላት ወደ ተሟላ ስራ ለመግባት እየሰራ ነው ብለዋል።

ኢዜአን ለማሻገር በተከናወኑ ተግባራት ሁሉ ድጋፍና ክትትል ላደረጉ የመንግስት አካላትና ሌሎች ባለድርሻዎችም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

በ1934 ዓ.ም የተመሰረተው ኢዜአ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም