ዕድሉን እንጠቀም…‼

82

ዕድሉን እንጠቀም…‼

በያንተስራ ወጋየሁ (ዲላ ኢዜአ)

በኢትዮጵያ ስር ሰዶ በቆየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመለየት፣ ከመፍታት ይልቅ በሚያባብሱ ቁልፉ ሀገራዊ ጉዳዮች ሁሉን አቀፍ፣ አካታችና አሳታፊ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው። የሀገራዊ  ምክክሩ የመጨረሻ ግብ የተረጋጋች፣  የበለፀገችና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን  እሙን ማድረግ ነው።

ከዚህም ባሻገር ብሄራዊ  ምክክሩ ለፖሊሲ አማራጮች፣ ለነባር ተቋማዊ ማዕቀፎች ና ለፖሊሲዎች ማሻሻያ የሚሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ለመጨረሻው ግብ መሳካት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይታመናል።በዓለማችን በርካታ ሀገሮች ብሔራዊ ምክክር አድርገው አለመግባባቶችን ከማጥበብ ባለፈ ንትሪክና ግጭት ሸኝተው ሰላምና መረጋጋትን አረጋግጠው ሀገራቸውን ከአደጋ ታድገዋል። በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ሀገርን ያከሰረ ህዝብን ደም ካቃባ ከአፋሙዝ ፍልሚያ ማግስት፣ በሰው ልጆች ታሪክ ተነግሮ የማያልቅ ግፍና መከራ ከተፈጸመ ቦኋላ ብሔራዊ ምክክርን አማራጭ የሰላም መንገድ አድርጎ መቀበል የተለመደ ነው።

በእርግጥ በትኛውም ጊዜ ሀገርና ህዝብ እስካለ ድረስ በብሔራዊ ምክክር አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት ረፍዶበት አያቅም። በተለይ ንብረትንም ነፍስን ከሚቀጥፍ የአፋሙዝ እሳት ተላቆ ተወያይቶ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማበጀት ተመራጭ የሰላም መንገድ ነው። ጥቂት የማይባሉ የዓለማችን ሀገሮች ብሔራዊ የምክክር መድረክ (National Dialogue) ሲሉት የተቀሩት ደግሞ እንደ ችግራቸው ስፋትና ጥልቀት ስያሜ በመስጠት አሳታፊና አካታች ውይይት በማድረግ ለሀገራዊ አለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮቻቸው እንዲሁም በታሪክ አጋጣሚ ለተፈጠሩ በደሎችና ግፎች መቋጫ አበጅተዋል። ምክክሩ የፈጀባቸው ጊዜና ያስገኘው ውጤት ቢለያይም ግብፅ፣ ማሊ፣ ቶጎና የመንን የመሳሰሉ ሀገሮች ብሔራዊ ምክክር ስልት፤ ደቡብ አፍሪካ፣ ሜክስኮና ኔፓልን የመሳሰሉት ደግሞ በችግራቸው ልክ ስያሜ በመስጠት የውይይት መድረኮችን አካሂደዋል።

የብሔራዊ ምክክሩ ስልጣንና ኃላፊነት አካታችነትና ገለልተኝነት እንዲሁም የመድረኮቹ ቅርፅና ይዘት በዋናነት ብሔራዊ ምክክር ያደረጉ ሀገሮች አከራካሪ ሆነው የተነሱ አጀንዳዎች መሆናቸውን፣ በዲላ  ዩኒቨርሲቲ በሦስተኛ ድግሪ መርሃ ግብር የብዝሃ ባህልና የአስተዳደር ጥናት ተማሪው ሄኖክ ንጉሴ ይናገራሉ። በአንድ ሀገር ብሔራዊ ምክክር ሲደረግ በሀገሪቱ ሰማይ ስር የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች የተለያዩ አስተሳሰቦች ያገባኛል የሚሉ ተቋማትና ግለሰቦች በነፃነት የሚሳተፉበትን አውድ መፍጠር፣ አሳታፊነት ከማረጋገጥና ለችግሮች የመጨረሻ መፍትሄ ማበጀት የብሔራዊ ምክክር መድረኮች ተፈጥሮአዊ ባህሪ ነው።በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ብዝሃ ባህልና አስተሳሰቦች ባሉባት ሀገር አካታችነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ይህም በእነዚህ መሰረታዊ ምክንያቶች ጠቃሚ ነው ሲሉም ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ምዕተ ዓመት የተከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች መሰረታዊ ምክንያታቸው ብዝሃነትን በኩል መልኩ ያለማስተናገድ ተጠቃሽ ማነቆ በመሆኑ ነው። ይህን ማነቆ  ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት በምክክር መድረኩ የሚገለል አካልና አስተሳሰብ እንዳይኖር መስራት ተገቢ ነው። በእርግጥ የሃሳብና የተግባር ልዩነቶችና አለመግባባቶች ባይኖሩ ብሔራዊ ምክክርም ባላስፈለገ ነበር። በመሆኑም ልዩነቶችን በእኩል መልኩ እንዲደመጡ መፍቀድና ምቹ ሁኔታ መፍጠር መብት ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህን በማስፈጸምና በመፈጸም በኩል መንግሥት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሁሉ በላይ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን የትኩረት ማዕከል ሊሆን ይገባል። በሌላ መልኩ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ለማበጀት አካታችነቱ ወሳኝ ነው።

መንግሥት የብሔራዊ ምክክር የማቋቋሚያ አዋጅ ከማውጣት አንስቶ ኮሚሽን ለማቋቋምና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ኮሚሽኑን የሚመሩ ኮሚሽነሮችን ለመሰየም የሄደበት ርቅት ገለልተኝነትና አካታችነትን በማረጋገጡ ረገድ ከወዲሁ ተስፋ የተጣለበት ነው። ይሁንና ለምክክር መድረኩ ህጋዊ ሥርዓት ከማበጀት አንስቶ አጀንዳዎችን በመቅረፅና በማስረፅ የምክክር መድረኩን ቅርፅና ይዘት በመለየት እንዲሁም ሂደቱን አሳታፊና ገለልተኛ በማድረግ ረገድ እ.አ.አ. ከ2013 እስከ 2014 የመን ላደረገችው ብሔራዊ የምክክር መድረክ (National Dialogue Conference) ውጤታማ ቅድመ ዝግጅት ብታደርግም ከውይይቱ በኋላ የተገኝው ውጤት ግን ሀገሪቷን ከብተና አላዳናትም።

ስለዚህ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ጥናቶች ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሄኖክ አሻግሬ በአድካሚ ሂደት የተገኝው ውጤት የተፈለገውን ሀገራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ይላሉ። በኢትዮጵያ ታሪክ የተፈጠሩ አለመግባባቶችና ቁርሾዎችን ለመፍታት የፖለቲካ ልሂቃንና ምሁራን የምክክር ሂደቱንም ሆነ ውጤቱን ከሚያደናቅፍ ነገር እጃቸውን ከመሰብሰብ ባለፈ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ገንቢ ሚና ሊጫዎቱ ይገባል።

የብሔራዊ የምክክር መድረኮች ከአደባባይ ይቅርታ አንስቶ ስልጣን እስከ መጋራት በደረሰ ውሳኔ መቋጫ አግኝተዋል። ይህም የራስን ጥቅም አስልቶ ከመምጣት ይልቅ የህዝብን ድምፅ ባከበረ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን መስራት የመላው ህዝብ ኃላፊነት ነው ይላሉ። ባንድራ በአንዲት ሀገር ስማይ ስር የሚገኙ ህዝቦችን የሚወክል ምልክት ነው። ህገ-መንግሥትም እንዲሁ። የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ ዕድገትና ብልፅግና ለማምጣት ጎታች የሆኑ አስተሳሰቦችንና ቁርሾዎችን በውይይት ፈትተን ወደ ልማት ፊታችንን ማዞር ወቅቱ የሚጠይቀው አስተሳሰብና ተግባር በመሆኑ ዕድሉን እንጠቀም …‼።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የዓድዋ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት  በዓደዋ፣ በማይጨው፣ በካራማራና በሌሎች አውደ ግንባሮች ያሳካነውን ድል በድህነትና በኋላቀርነት እንድገመው። ቸር ወሬ ያሰማን!! ሠላም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም