በአማራ ክልል ከ40ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ40ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ ለምቷል

ባህር ዳር፣ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ ወራት እስካሁን ድረስ ከ40ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዞን ዘንዘልማ ቀበሌ በበጋ መስኖ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ማሳ እየጎበኙ ነው።
ጉብኝቱ በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን የማጠናከር፤ የተስተዋሉ እጥረቶችን ደግሞ በማረም ልማቱን ተስፋፍቶ እንዲቀጥል የማበረታታት ዓላማ እንዳለው የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሀይለማርያም ከፍያለው ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ አሁን በያዘው አግባብ የበጋ መሰኖ ስንዴ ልማትን አጠናክሮ ከቀጠለ በቀጣይ ከውጭ አገር የሚገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረት እንደ ሀገር የተያዘውን ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሃላፊው እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወራት እስካሁን ድረስ ከ40ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ ለምቷል።
ባለፈው ዓመት በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ለመጀመሪያ ጊዜ 13 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱ ታውቋል።
በየዓመቱ ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ ለማስገባት 700 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዘንዘልማ ቀበሌ በበጋ መስኖ 300 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታገጠም እየለማ ሲሆን በዚህ የጉብኝት መረሃ ግብር የፌደራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው።