የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ፍኖተ ካርታ በደቡብ ክልል ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

168

ጂንካ፤የካቲት 24/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል በሙከራ ደረጃ የተጀመረው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ፍኖተ ካርታ በመጪው ዓመት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በትምህርት ጥራት ችግሮች ዙሪያ ከትምህርት ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጂንካ ከተማ በመከረበት ወቅት እንደተመለከተው፤ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ፍኖተ ካርታ በሙከራ ደረጃ በክልሉ በ115 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  እየተተገበረ ነው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በወቅቱ እንዳሉት  ባለፉት ስድስት ወራት በትምህርት ተደራሽነትና በተማሪዎች ምዝገባ የተሻለ አፈፃፀም  ተመዝግቧል።

በክልሉ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱት መካከል  95 በመቶ የሚሆኑ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ቢሮው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ቢሰጥም  ኩረጃ   አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል።

መምህራን የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሙያዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተው፤ ኩረጃን የሚጸየፍና በራሱ የሚተማመን  ትውልድ የማፍራት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡም አሳስበዋል።

መምህራን እራሳቸውን በስልጠና ማብቃትና ደረጃቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው ጠቁመው፤  ዘመኑ የሚፈልገውን እውቀት ኖሯአቸው ተማሪዎቻቸውን ማገዝ እንዲችሉ የቴክኖሎጂ ትስስራቸውን ማጎልበት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

አዲሱ የትምህርት ስርዓት ፍኖተ ካርታ በሙከራ ደረጃ መጀመሩን ጠቁመው፤ የትምህርት ጥራቱ ስኬታማ እንዲሆን ጠንካራ ተሳትፎ መደረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በክልሉ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ያለው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ፍኖተ ካርታ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየታየበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በትምህርት ቢሮው የስርዓተ ትምህርት ዘርፍ ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ሳሙኤል ናቸው።

''ስርዓተ-ትምህርቱ ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ለችግሮቻችን ወደ ውጭ ከማተኮር  ይልቅ በራሳችን አቅም መፍታት እንድንችል አቅም ይፈጥርልናል'' ብለዋል።

የባለድርሻ አካላት ሚና በግልጽ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ለትምህርት ጥራት ችግር መፍትሄ እንደሚያመጣ ገልጸው፤ በተለይም ወላጆች ፣ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የትምህርት ቢሮው ምክትል ኃላፊው አቶ ተስፋዬ ደፋሩ በበኩላቸው፤ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ ካጋጠሙ ችግሮች አንዱ የመፅሐፍ እጥረት ነው  ብለዋል።

 የሙከራ ትግበራው ለውጦች በመገምገም በ2015 ዓ.ም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተፈጻሚ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ  መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም