ኮርፖሬሽኑ ከግል ባለኃብቶች ጋር በሽርክና 15 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት የፍላጎት መግለጫ ጨረታ አወጣ

178

አዲስ አበባ፣  የካቲት 24/2014(ኢዜአ)  የፌዴራል የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ 15 ሺህ ቤቶችን ከባለኃብቶች ጋር በሽርክና ለመገንባት የፍላጎት መግለጫ ጨረታ አወጣ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ ከግል ባለሃብቶች ጋር በሽርክና 15 ሺህ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመገንባት አቅዷል።

ጎን ለጎን ሦስት የስብሰባ ማዕከላትና ሁለት የፈረስ መጋለቢያ ቦታዎችን ለመገንባት መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ በግንባታ ለመሳተፍ አቅም ያላቸው የዘርፉ ኩባንያዎችም በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንት አቅራቢነት መሳተፍ ይችላሉ ብለዋል።

በተለይም የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በተናጠልና ከውጭ አገር ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ተጣምረው በግንባታው መሳተፍ እንደሚችሉም ነው የገለጹት።

በግንባታው የሚሳተፉ ኩባንያዎች በቀዳሚነት በዘርፉ ከአሥር ዓመታት በላይ በዘርፉ የተሳተፉና ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ በአንድ ፕሮጀክት ያንቀሳቀሱ መሆን አለባቸው ብለዋል።

ኩባንያዎቹ አዲስ የዘርፉን ቴክኖሎጂ የሚያስተዋውቁና የውል ስምምነት በገቡ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ የሚገቡ ከሆነ በጨረታው መሳተፍ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ኩባንያዎቹ ከመንግሥት ምንም አይነት ዋስትና ሳይጠይቁ አዲስ የውጭ ፋይናንስ በራሳቸው ማቅረብ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸውም አብራርተዋል።  

በግንባታው ለመሳተፍ የሚፈልጉ ኩባንያዎች እስከ መጋቢት 21/2014 ዓ.ም ድረስ የፍላጎት መግለጫቸውን ለኮርፖሬሽኑ በማስገባት በጨረታው መወዳደር እንደሚችሉ ገልጸዋል።  

ለዚህም CEOoffice@lbdc.gov.et የኢ-ሜይል አድራሻ በመጠቀም መረጃቸውን እንዲያስገቡ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በሕዳር 2015 ዓ.ም በቤት ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአይ ሲቲና በግብርና ልማት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ለማካሄድም እቅድ ይዟል።

የፌዴራል የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በከተሞች የቤቶች ልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

በገጠር አካባቢዎች ከግብርና ልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ጥናት እያደረገ ነው።  

የፌዴራል ተቋማትና የልማት ድርጅቶችን የመሬት ይዞታ መረጃ በመሰብሰብ የማጥራት፣ ልኬታቸውን የማወቅና የዳታ ቤዛቸውን የማስተዳደር እንዲሁም ጥቅም ላይ የዋሉና ያለሙ ሥፍራዎችን  በመለየት ወደ ሥራ ለማስገባት እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም