በዞኑ የኢንቨስትመንት ውል ፈጽመው ወደ ስራ ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

65

መተማ፣  የካቲት 24/2014 (ኢዜአ )በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ የኢንቨስትመንት ውል ፈጽመው ወደ ስራ ባልገቡ 35 ባለሃብቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ተፈሪ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማ ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማስፋፋት ታስቦ  127 ሄክታር መሬት በኢንዱስትሪ መንደር ተዘጋጅቶ 53 ሄክታሩ ለባለሀብቶች ተላልፏል።

ቦታ ከተሰጣቸው ውስጥ ዘጠኙ ባለሃብቶች የተሰጣቸውን 70 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ለሁለት ዓመት ያህል ያለምንም ልማት አጥረው በማስቀመጣቸው  እንዲመልሱ መደረጉን ተናግረዋል ።

ባለሃብቶቹ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ በብረታ ብረት፣ በዘይት ፋብሪካ፣ በኬሚካልና በጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ለመሰማራት ውል ወስደው እንደነበር አስታውሰዋል።

በገቡት ውል መሰረት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደጋጋሚ ግፊት ቢደረግም ቦታውን አጥረው ከማስቀመጥ ውጭ ማልማት ባለመቻላቸው መሬቱን እንዲመልሱ መደረጉን  አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በተሰጣቸው ቦታ ግንባታ ብቻ በማካሄድ  ከ2 እስከ 5 ዓመት ማምረት ያልጀመሩ  26 ባለሃብቶች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል።

ባለሃብቶቹ በምደባ በተረከቡት ቦታ ግንባታ ገንብተው በግንባታው ከተለያዩ ባንኮች ብድር ቢወስዱም  የታሰበውን ልማት ያላሳኩ መሆኑን አብራርተዋል።

ባለሃብቶቹ 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ቢያስመዘግቡም ወደ ስራ እንዲገቡ ተከታታይ ድጋፍና እገዛ ቢደረግላቸውም መግባት ባለመቻላቸው ለሁለተኛ ጊዜ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለሃብቶች ቀደም ሲል በምክንያትነት ያነሱት የነበረው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦትና የፀጥታ ሁኔታ መሻሻሉን የጠቀሱት ሃላፊው አሁን በተሰጣቸው እድል ወደ ማምረት የማይገቡ ከሆነ ወደ ክስ የሚገባ መሆኑን አመላክተዋል።

በሰሊጥ ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት ውል ወስደው ግንባታ ካጠናቀቁ ከ2 ዓመት በላይ ቢሆናቸውም በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግርና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት ወደ ስራ መግባት ሳይችሉ መቆየታቸውን የገለፁት ደግሞ አቶ ሞላልኝ መኩሪያ ናቸው።

በማቀነባበሪያ ፋብሪካው ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውንና ፋብሪካው  ከ70 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

አሁን ላይ የፀጥታው ሁኔታ መሻሻሉና የሃይል አቅርቦት እጥረቱም በመፈታቱ በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ሌላኛው ባለሃብት አቶ ዳዊት ዘሪሁን በበኩላቸው በጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ዘርፍ ለመሰማራት ውል ወስደው 6 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክበው ግንባታውን ከሶስት አመት በፊት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በወቅቱ በአካባቢው የነበረው የሰላም ችግር ወደ ስራ እንዳይገቡ እንቅፋት ሆኖ የቆየባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሌላኛው ምክንያት ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም አሁን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት ችግሩ የሚፈታ በመሆኑ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገቡ አመላክተዋል።

በኢንዱስትሪ መንደሩ 75 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ያሉ ሲሆን በተሟላ መንገድ ወደ ማምረት ሲገቡ ከ9 ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በቋሚና በጊዜያዊነት የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም