የዩክሬንን ጉዳይ ሁሉም ወገኖች ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች

65

የካቲት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዩክሬን ጉዳይ ሁሉም ወገኖች ነገሮችን በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዩክሬን ጉዳይ ለሁሉም ወገኖች በጻፉት ደብዳቤ ያለፉት ሁለት አመታት ሁኔታዎች የአለም እርስ በርስ ትስስር የተንጸባረቀበት ነው፤ በአለማችን በሚነሱ የትኛውም ጉዳዮች የጉዳዩ ተቋዳሽ የማይሆን ሀገር እንደሌለ በሁለቱ አመታት የተከሰቱ ሁኔታዎች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ለዚህም ኮቪድ-19 በተከሰተ ጊዜ ተጽዕኖው በእያንዳንዱን የአለም ክፍልና ህዝብ ላይ መድረሱ ነው ሲሉ አመልክተው፤ በጤና ላይ በደረሰውም ሆነ በጦርነቶች ምክንያት በደረሱ ጉዳቶች ኢትዮጵያ በሁሉም ችግሮች ተጎጂ እንደሆነ ሀገር ሁኔታዎችን የበለጠ ትገነዘባለች ብለዋል።

በጦርነት ውስጥ መቆየት የሚያስከፍለውን ዋጋም ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት ጦርነት እንደምትረዳው አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጦርነት በኢኮኖሚ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰቡና በአጠቃላይ በእያንዳንዱ የሕይወት ሂደት ውስጥ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጎጂነት ኢትዮጵያ እንደምታውቀው ገልጸዋል።

በአሁንም ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን ጦርነት ባስከተለው ተጽእኖ ስር መሆናቸውንም አመልክተው፤ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓ ወዳጅ ሀገር ሁሉም አካላት በዩክሬን የተከሰተውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የተከሰተው ችግር የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍተታት ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ይገባቸዋል ሲሉ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ አለም አቀፍ መርሆችን በጠበቀው፣ ሉአላዊነትን ባከበረውና የሁለትዮሽ ጥቅምን ባስጠበቀው ዲፕሎማሲያዊ መርኋ ነገሮች በሰለማዊ መንገድ እንዲፈቱ ድጋፏን እንደምታደርግም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም