"የነፃነት ዋጋ የሚለካው ነፃነት የተነፈጉ አገሮችን ታሪክ ስንመረምር ነው"

73

የካቲት 23/2014(ኢዜአ)  "የነፃነት ዋጋ የሚለካው ነፃነት የተነፈጉ አገሮችን ታሪክ ስንመረምር ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ126ኛው የአድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዝዳንቷ በዚህን ወቅት  "አያት ቅድመ አያቶቻንን በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የቀረበላቸውን ጥሪ በመቀበል ከቅኝ ተገዥነት ሞት ይሻላል ብለው ለአገራቸው ነፃነት ውድ ህይወታቸውን ገብረዋል" ብለዋል፡፡  

ኢትዮጵያዊያን የነፃነታቸውና የአሸናፊነታቸው ምልክት አድርገው የሚያከብሩት የአድዋ ድል በዓል ከ126 ዓመት በፊት በነበረው ትውልድ የተፈጸመ ጀብዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአድዋ ድል ለነፃነትና የአገር ሉዓላዊነት ተብሎ የተከፈለ ውድ መስዋዕትነት መሆኑን የምናውቀው የአድዋ አርበኞች በአይበገሬነት ስሜት የከፈሉትን ዋጋ ስንረዳ ነው ብለዋል፡፡

"የነፃነት ዋጋ የሚለካው ነፃነት የተነፈጋቸው አገሮችን ታሪክ ስንመረምር ነው" ያሉት ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ፤ የአደዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ጥቁር ህዝብ ማሸነፍ እንደሚችል ለዓለም በተግባር ያሳዩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም" እንዲሉ፤ አድዋንና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የየዘመኑ ትውልዶች የፈጸሙት ገድል መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ከድህነት ለመውጣት በአንድነት መቆም መግባባትና መናበብ እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ በአንድነት ከተባበርን የሚያቆመን እንደሌለ ከአድዋ ድልና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መማር አለብን ብለዋል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው በአድዋ ጦርነት ወቅት 100 ሺህ አርበኞች ወደ ወረኢሉ ሲከቱ በቋንቋ ባይግባቡም በኢትዮጵያዊነታቸው ቅንጣት ታክል ልዩነት አልነበራቸውም ብለዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን መንፈሰ ጠንካራና ኩሩ ህዝቦች በመሆናችን ከአባቶቻቸን የተረከብነውን ገድል ዛሬም መድገም ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ጀግንነት የሚለካው በጦርና በጎራዴ ብቻ መሆን የለበትም ያሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፤ ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከጦርነት በኋላ በፍቅርና በአንድነት አብሮ በመኖር አሸናፊ መሆን አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም