በኦሮሚያ ክልል የውሃ ልማት ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

የካቲት 22/2014/ኢዜአ/  በኦሮሚያ ክልል የውሃ ልማት ዘርፍን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የክልሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።

የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የኦሮሚያ ፕላስቲክ ቱቦ ማምረቻ ድርጅትን ጎብኝተዋል።

በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የመንግስት ሃብት አስተዳደር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት የውሃ ዘርፉን በማልማት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ኢትዮጵያ በርካታ የውሃ ሐብት ባለቤት ብትሆንም ይህንን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር አሁንም ብዙ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም  ከወራጅ ወንዝም ሆነ ከከርሰ ምድር የሚወጣ የውሃ ሃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያግዙ ግብዓቶችን ማምረት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የኦሮሚያ ፕላስቲክ ቱቦ ማምረቻ ድርጅት  ለመስኖ፣ ለመጠጥ ውሃ እና ለንጽህና መጠበቂያ  የሚያገለግሉ የውሃ ማስተላለፊያ ምርቶችን በማቅረብ በዘርፉ ተደራሽነትን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ፋብሪካው ከጥሬ እቃ ችግር ጋር በተያያዘ በሙሉ አቅሙ እየሰራ አለመሆኑን ጠቁመው፤ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም  በክልሉ ሌሎች ተመሳሳይ ፋብሪካዎችን በማስፋፋት በውሃ ልማት ላይ እየተካሄዱ ያሉትን ተግባራት የማጠናከር ሥራ እንደሚቀጥልም  ነው ያረጋገጡት፡፡

የፋብሪካው  ዋና ዳይሬክተር አቶ ዱጉማ ኢሬሶ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው ከውጭ የሚገቡ የፕላስቲክ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ነገር ግን ባለበት የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በግማሽ አቅሙ እያመረተ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ፋብሪካው  ለ170 ሰዎች ቋሚና ለበርካታ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም