የንግድ ህጉን በተላለፉ ከሁለት ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

58

ጎንደር ፤ የካቲት 22/2014(ኢዜአ) በከተማው የንግድ ህጉን በተላለፉ ከሁለት ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ  እርምጃ መወሰዱን የጎንደር ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለጸ ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬ እንደገለጹት እርምጃው የተወሰደው በሚዛን ልኬት በማጭበርበር፤ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን እሽግ ምግብና መጠጦችን በመሸጥ፤ የፍጆታ ምርቶችን አላግባብ ደብቆ  በማከማቸትና ያለ ንግድ ፈቃድ በመነገድ  ነው፡፡

በህገ-ወጥ ነጋዴዎቹ ላይ  የንግድ ድርጅቶቹን የማሸግ፣ የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያን ጨምሮ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዱን ያመለከቱት ሃላፊው፤ በ17 ነጋዴዎች ላይ ደግሞ በፍርድ ቤት ክስ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡

መምሪያው ህግ የማስከበር ሥራውን እንደሚያጠናክርና ህብረተሰቡም  ህገ ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን በመጠቆም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ በምርቶቹ ላይ የተጻፈ የመጠቀሚያ ጊዜ ተፍቆ በላዩ ላይ ሀሰተኛ የማጭበርበሪያ የንግድ ምልክቶች ጭምር ተለጥፎ እንደሚያጋጥም አመልክተዋል፡፡

በሚዛን ልኬት በሚያጭበረበሩና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምግብና መጠጦች እየሸጡ የሚገኙ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም