ሁለት የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

70

ጅማ፣  የካቲት 22/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጅማ ቅርንጫፍ ሁለት ሰራተኞች ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የጅማ ከተማ ወረዳ ሁለት ፖሊስ መምሪያ የሙስና የወንጀል መርማሪ ሳጂን ምስጋና ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለቱ የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች 360ሺህ ብር የቀረጥ እዳ አለብህ በሚል አንድ የቅርንጫፉን ግብር ከፋይ ነጋዴ ተገቢነት የሌለው ክፍያ ጠይቀዋል።

ግብር ከፋዩ ነጋዴም ለምን ይህን ያክል ገንዘብ እከፍላለው በማለት ይከራከራሉ።

ሁለቱ የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞችም እንግዲያውስ ለኛ 70 ሺህ ብር ክፈለንና እናስቀርልሀለን በማለት ከነጋዴው ግለሰብ ጋር  በስልክ ይስማማሉ።

ነጋዴው 70 ሺህ ብር መክፈል አልችልም በሚል በድርድር 50ሺህ ብር እንደሚከፍላቸው ተስማምተው የጊዜና ቦታ ቀጠሮ ያመቻቻሉ።

በቅርንጫፉ የስራ ሀላፊ የሆነው ተጠርጣሪ በስልክ በተደረሰ ስምምነት መሰረት ገንዘቡን ከነጋዴው እንዲቀበል ሌላውን ተጠርጣሪ የስራ ባልደረባውን ይልከዋል።

ነጋዴው ጉዳዩን ቀድመው ለፖሊስ በማሳወቅ ዮርዳኖስ በተባለ ሆቴል የካቲት 18 ቀን 2014 ዓም በቀጠሯቸው መሰረት ተገኝተዋል ።

ተጠርጣሪው የቅርንጫፉ ሰራተኛም በቀጠሮው መሰረት ከሆቴሉ በመድረስ  ከነጋዴው በፖስታ የተጠቀለለ 40ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ይያዛል።

አንደኛው ተጠርጣሪ በዚህ መልኩ እጅ ከፍንጅ ሲያዝ ሌላኛው ተጠርጣሪ የስራ ሀላፊ ከሚሰራበት ጉምሩክ ኮሚሽን ጅማ ቅርንጫፍ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ገንዘቡን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተጠርጣሪ  የፖሊስ አባላትን "ገንዘቡን ውሰዱና ልቀቁኝ" በማለት  በገንዘብ ለማማለል መሞከሩን ሳጂን ምስጋና ተፈራ ገልጸዋል።

የተጠርጣሪዎቹ የምርመራ መዝገብ ለአቃቤ ህግ ተላልፎ ጉዳያቸው በጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ መሰል የሙስና ወንደሎችን በማጋለጥ የህግና የእውነት ተባባሪ እንዲሆን ያስፈልጋል ሲሉ ሳጂን ምስጋና ተፈራ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም