የአድዋ ድል ቱሩፋቶች ምንድን ናቸው?

የአድዋ ድል ቱሩፋቶች ምንድን ናቸው?

"የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ሕብረት፤ የአፍሪካ የነፃነት ጮራ" በሚል መሪ ሐሳብ ለ126ኛ ጊዜ የሚከበረው የአድዋ ድል ክብረ በዓል ሲምፖዚየም ተካሂዷል።

የአድዋ ድል ፓን-አፍሪካዊነት እንዲጎለምስ ስላበረከተው ሚና መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤሜሬተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፤ ከአድዋ ድል በፊት የኢትዮጵያዊነት ንቅናቄ እንደነበር ገልጸዋል።

ከአድዋ ጦርነት ክስተት ደግሞ ይህን መንፈስ አጽንቷል፤ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ቅኝ ግዛት ነው፤ የነጮች ደግሞ የገዥነት የሚለውን እሳቤ ሽሯል ብለዋል።

በአድዋ ድል የኢትዮጵያ የጦር መሪ አፄ ምኒልክ ዝና በዓለም እንዲናኝ፣ የአድዋ ጀግኖች ለጥቁሮች አርዓያ እንዲሆኑ አስችሏልም ነው ያሉት።

የአድዋ ድል እርሾ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቆይቶም የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ እንዲቋቋም እና ኢትዮጵያም የአፍሪካ እምብርት ሆና እንድትቀጥል የአድዋ ድል ሚና እንደነበረው ያስረዳሉ።

በአሜሪካ፣ በሐይቲ፣ በአውሮፓ፣ በካሪቢያን የሚገኙ ጥቁሮች ዘንድ የፓን-አፍሪካዊነት እንቅስቃሴ እንዲያብብ፣ ኢትዮጵያም የጥቁሮች የነጻነት ትግል ፋና ወጊ እንድትሆን ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

በ1928 የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በርካታ አፍሪካ አሜሪካኖች ከገንዘብ ማዋጣት እስከ ወዶ ዘማችነት ለመቀላቀል እንቅስቃሴ ስለማድረጋቸው፣ በአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች የኢትዮጵያን መወረር ተቃውመው በየአገራቱ ተጽዕኖ መፍጠራቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም የአድዋ ድል የቅኝ ግዛት ሰንሰለትን በጥሷል፤ ኢትዮጵያንም የነጻነት ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏል ይላሉ ፕሮፌሰር ባሕሩ።

'የአድዋ ድል ለአሁኑ ትውልድ ያበረከታቸው ቱሩፋቶች' በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት የመከላከያ ሰራዊት ባልደረባ ኮሎኔል መስፍን ለገሠ አድዋ ለትውልዱ ስላበረከተው ሚና አትተዋል።

ከአድዋ ቱሩፋቶች መካከል አንዱ ለሌላው የሞተበት፤ የሰውነት ክብራችንና ኢትዮጵያዊነታችንን ያጸና፤ በነጻነት ያለመደራደርን፣ ጀግንነትንና አልሸነፍ ባይነትን እንዲሁም ሌሎችን ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት በተሰለፈበት ዐውደ-ውጊያ ሁሉ አሸናፊነትን እንዲጎናጸፍ ያስቻለውን ጀግንነት አላብሰውት ከዘለቁት ሚስጢሮች መካከል የአድዋ ድል ቱሩፋት አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን መተባበርና አንድነትን ማውረሱን፣ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ የነጻነት ተምሳሌት ማድረጉንና የኢትዮጵያዊያንን የአስተሳሰብ ልዕልና ባለቤትነታቸውን ያሳየ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በጦርነቱ የምርኮኞች አያያዝና እንክብካቤ ኢትዮጵያዊያን አልሰለጠኑም የሚለውን የወራሪዎች አመለካከት የቀየረ እንደነበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም