በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል አባላት ፓርቲው ያከናወናቸውን ተግባራት የሚገመግም ጉባኤ እያካሄዱ ነው

57

ሀዋሳ፤ የካቲት 22/2014 (ኢዜአ)፡ በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል አባላት ፓርቲው ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚገመግም ጉባኤ በ17 ማዕከላት እየተካሄደ መሆኑን በፓርቲው የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አስታወቀ።
የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ፓርቲው ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚገመግም ጉባኤ በ17 ማዕከላት እየተካሄደ ነው።

ባለፉት ዓመታት ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

''እኔ ካልመራሁ ሀገር ትፈርሳለች በሚል እሳቤ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ከውጪ ኃይሎች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ ያደረጉትን ሙከራ መላውን ህዝብ በማነቃነቅ መመከት የተቻለበት ጊዜ ነበር'' ብለዋል።

ብልፅግና ውህድ ፓርቲ ሆኖ ከተደራጀ በኋላ በክልሉ በውስን አባላት ዘንድ ወጣ ገባ የማለት አዝማሚያዎች ይታዩ እንደነበር አስታውሰው፤ አባላቱን ለማጥራት ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የአባላት የተሳተፉበት ግምገማ መደረጉን አስታውሰዋል።

ኃላፈው እንዳሉት ከ10 ሺህ 400 በላይ መሰረታዊ ድርጅቶችና ከ60 ሺህ በሚበልጡ ህዋሳት በተካሄደው ግምገማ የጎላ ችግር የታየባቸውን አባላትና አመራሮችን የማገድና የማሰናበትና የፓርቲውን አደረጃጀት በአዲስ መልክ የማዋቀር ስራ ተሰርቷዋል።

የውይይት ሰነድ በማዘጋጀት በክልል ደረጃ ከየካቲት ከትናንት ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ክልል አቀፍ የፓርቲው ጉባኤ እየተካሄደ መሆኑንም አመልክተዋል።

በጉባኤው ፓርቲውን በመወከል ከመጋቢት 2 ጀምሮ "ከፈተና ወደ ልዕልና" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የብልፅግና ጉባኤ  የሚሳተፉ አባላት ምርጫ ይካሄዳልም ብለዋል።

በዚህም  በሀገር አቀፉ የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የሚሳተፉ 278 የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአርሶ አደሮች፣ የአርብቶ አደሮች፣ የምሁራንና የሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ምርጫ እንደሚደረግና ከመካከላቸው 253 በጉባኤው በድምፅ የሚሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም