የአድዋ ድል የሀገር ፍቅርና መተባበር ውጤት ነው - ወጣቶች

90

ሀዋሳ፤ የካቲት 22/2014 (ኢዜአ) የሀገር ፍቅርና የመተባበር ውጤት የሆነው የአድዋ ድል ሁሉም ልዩነቱን በማጥበብ ኢትዮጵያን በሚያሻግሩ ጉዳዮች ላይ እንድያተኩር የሚያስተምር መሆኑን በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ።
ድሉ  የአሁኑን ትውልድ በተለያየ መንገድ ሊያስተምሩ የሚችሉ በርካታ ታሪኮች የተመዘገቡበት እንደሆነ ነው ወጣቶቹ ያመለከቱት፡፡

ወጣት አወል መሐመድ እንዳለው፤ በአድዋ ድል የተመዘገበው የአባቶቻችን ጀግንነት የአሁኑ ትውልድ እንደታሪክ የሚናገረው ብቻ ሳይሆን ሊማርበት የሚገባው ትልቅ ትምህርት ነው።

የአድዋ ድል በየዘመኑ እየተቀያየረ  ለሚመጣ የተለያየ ጠላት ትምህርት ያኖረ በመሆኑ አሁን እንደ ሀገር ከገጠመን ፈተናም የምንወጣው አባቶች አሸናፊ የሆኑበትን የአንድነት ሚስጢር በመጠቀም ብቻ ነው ሲል ገልጿል።

በኢትዮጵያዊ አንድነትና መተባበር የተገኘውን የአድዋን አኩሪ ድል ሲታሰብ  አሁን እየታየ ያለውን ልዩነት በማጥበብና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ሊሆን እንደሚገባ  አመልክቷል።

አድዋ የጥቁሮችን የባርነት ቀንበር የሰበረ በመሆኑ  ኩራት እንደሚሰማው የተናገረው ወጣቱ፤ የተባበር ክንድ ምን ያህል አቅም እንዳለው  እንድማር አድርጎኛል ብሏል ወጣት አወል።

ከጫፍ እስከ ጫፍ ኢትዮጵያዊያንን ያስነሳው የሀገር ፍቅርና ቅን ልቦና ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያመለከተው ዋጠቱ፤ ''ታሪካችንን በማወቅ፣ማንነታችንን በመረዳትና   ህጸጾቻችንን  በማረም ሃፊነታችን እንወጣ'' ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ቀኑ ሲታሰብ ዘመን የማይሽረውን የአድዋን ታሪክ ትውልድ እየተቀባበለ ማሳደግ በሚያስችሉ ሁነቶች መሆን እንዳለበትም ጠቁሟል፡፡

''ከአድዋ ድል የአሁነት ትውልድ ሊማር የሚገባው አንድነትን ነው'' ያለው ደግሞ  ወጣት መስፍን መሸሻ ነው፡፡

አባቶች ዘመናዊ መሳሪያ ሳይታጠቁ ኢጣሊያንን ድል የነሱበት የአድዋ  ድል በሀገር ጉዳይ ያላቸውን መተባበርና አቅም ለመላው ዓለም ያሳየ መሆኑንም ተናግሯል።

የአድዋ ድል የራሳችንን ቋንቋ ከመናገር ጀምሮ በቱባ ባህሎቻችን እንድንኮራ  ያደረገ  ብዙ ዋጋ የተከፈለበት አኩሪ ገድል በመሆኑ ወጣቱ በማህበራዊ የትስስር ገፆች  ጭምር ታሪካችንን ማጉላት አለብን ነው ያለው።

ወጣት መቅደስ ታደሰ በበኩሏ፤ በፍቅርና አንድነት ከተገኘው  የአድዋ ድል  የአሁኑ ትውልድ ልንማርበት   ይገባል ስትል ገልጻለች።

 የአድዋ ድል መተባበርን ወደ አሸናፊነትን የሚያመጣ መንገድ መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ መሆኑን የጠቀሰችው ወጣት መቅደስ፤  የአባቶቻችንን መንገድ በመከተል ይህንን መጥፎ ጊዜ ማለፍ ይገባናል ብላለች።

ሁሉም በያለበት የስራ መስክ ጠንክሮ በመስራት  ሀገራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት የአድዋ አባቶችን ጥንካሬ መድገም እንደሚኖርበትም አመልክታለች፡፡

''ስለ አድዋ ድል ሳስብ ከሌሎች ጥቁር ህዝቦች በተለየ ሁኔታ ኩራት ይሰማኛል'' ያለው ደግሞ  ሌላኛው የሀዋሳ ነዋሪ ወጣት ሮቤል ጌታቸው ነው፡፡

''የጥቁር ህዝቦች መገለጫ የሆነችው ኢትዮጵያ በአድዋ የፈጸመችው ገድል በመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት የተገኘና አሁን ላለው ትውልድ ትምህርት ሊሆን የሚችል ነው'' ብሏል፡፡

ወጣቱ አድዋን ሲያስብ አሁን በየአካባቢው ከሚታየው መከፋፈል ወጥቶ አንድነት ላይ ቢዘምትና ለሁሉም ችግር መፍትሔ ወደ  ሆነው መነጋገር መምጣት መቻል እንዳለበት አስተያየቱን ሰጥቷል።

''የሀገር ሰላም ከሁሉም ይቀድማል ያለው'' ወጣቱ፤  የሀገር መጻኢ እድል  በወጣቱ  እጅ በመሆኑ የአድዋ ድል ቀንን እንደነጻነት ዕለት እያከበረ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሀገር ሉዓላዊነት እና ነጻነት እንደማይደራደሩ ያስመሰከሩበት አንጸባራቂው የአድዋ ድል 126ኛው ዓመት ነገ በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም