የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከሩ ተገለጸ

58
አክሱም ነሀሴ 27/2010 የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ያደረጉት የሰላም ስምምነት ተከትሎ  በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡ ከመረብ ለኸ ወረዳ የተወጣጡ ነዋሪዎች በሁለቱም ድንበር ላይ በሚገኝ መረብ ወንዝ  ድረስ በመጓዝ ለወንድም ኤርትራዊያን ለሰላም ያላቸውን ዝግጁነት ፣ አክብሮትነና ፍቅራቸውን  ገልጸውላቸዋል፡፡ በወረዳው  የምሕቋን ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አቶ ገብረማርያም አረጋይ በዚህ ወቅት ለሀያ ዓመታት ተለያይተው ከቆዩት ወንድም ህዝብ ጋር እርቀ ሰላም ወርዶ  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ " ከወላጆቻን እና ወንድሞቻችን ጋር ተለየያይተን ቆይተናል፣ እስከ አሁን የተጎዳነው  ይበቀናል "ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝደንት ኢሳያስ  አፈወርቂ  የጀመሩት የሰላም ጥረት ተከትሎ ሁለቱም ህዝቦች ግንኝነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡ ላለፉት ዓመታት ተዘግቶ የነበረ የመረብ ድንበር አሁን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየታየበት መሆኑን ጠቅሰው የተጀመረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን  የህዝብ  ለህዝብ ግንኙነቱ ለማጎልበተ ሁለቱም መንግስታት የጀመሩት  ጥረት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡ " አንድነታችን እና ሰላማችን በአዲሱ ዓመት ይታደሳል "ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌ ገበሬ ማህበሩ  ነዋሪ ቄስ  ብርሃነ ገብረመስቀል ናቸው፡፡ ፍላጎታቸው ሰላም ፣አንድነትና ፍቅር  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝደንት ኢሰያስ  አፈወርቅ ያደረጉት የሰላም ስምምነት በመቀጠል  ድንበር አካባቢ በሚገኙ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች  ትልቅ ለውጥ  መታየቱንም አመልክተዋል፡፡ በድንበር አካባቢ ያሉት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተገናኝተው መወያየት እንደጀመሩ የጠቆሙት ቄስ  ብርሃነ ገበያቸውና እምነታቸው የሚያመልኩበት ቦታም አንድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተፈጠረው አለመግባባት ላለፉት ሀያ ዓመታት ዋና ተጎጂውም ድንበር አካባቢ የሚገኙ ህዝቦች መሆናቸውንና ሰላማዊ ግንኝነቱ  ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ቄስ  ብርሃነ ተናግረዋል። የራማ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ታሕጓስ ገብረ በበኩላቸው " ህዝብ ሰላም ፈላጊ ህዝቦች መሆናችንን ለመግለጽ ባለፉት ቀናት በድንበር መረብ ወንዝ ድረስ  ተጉዘን  ዝግጅነታችን ለኤርትራውያን ወንድሞቻችን ገልጸንላቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ ህዝቦች በባህልና ቋንቋ ተመሳሳይ መሆናቸውን ጠቅሰው ያለፈውን አስቸጋሪ ጊዜ በመርሳት ተያይዘው የሰላምና ልማት ጉዞ  ማስቀጠል እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ "ሰርተን ልንለወጥና የሀገራችን እድገት ለማስጠል አዲስ  ታሪክ ሰርተን እንድናልፍ ትልቅ ስራ ይጠብቅብናል " ብለዋል። ወይዘሮ ታሕጓስ  ላለፉት 20 ዓመታት ግንኙነቱ ተቋርጡ የነበረው ግንኙነት ለማስቀጠል ተሻግረው የኤርትራ መሬት በመርገጣቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸውም  ገልጸዋል። በመረብ፣ ዘላአምበሳ ናታሕታይ አድያቦ ድንበር አዓባቢ የሚገኙ ህዝቦች ለ20 ዓመታት የነበረው ችግር ተቀርፎ በማየቱ  አዲስ ታሪክ  ነው" ያለው ደግሞ  በመረብ ለከ ወረዳ የጭላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሓለፎም ብርሃነ ነው። በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች  የዘመን መለወጫ በዓልን በጋራ ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም