የብልፅግና ፓርቲ የመሠረታዊ ፓርቲ የቅድመ ጉባዔ ኮንፈረንስ በሐረሪ ክልል እየተካሄደ ነው

121

ሐረር፤ የካቲት 22/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ አባላት የተሳተፉበት የመሠረታዊ ፓርቲ የቅድመ ጉባዔ ኮንፈረንስ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የፓርቲው የክልሉ ጽህፈት ቤት ገለጹ።
ኮንፍረንሱ እየተካሄደ ያለው  በሁሉም የክልሉ ቀበሌዎች  በሚገኙ   የፓርቲው አደረጃጀት  መሆኑን የጽህፈት ቤቱ  ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሐመድ አስታውቀዋል።

በክልሉ ከ30 ሺህ  በላይ የፓርቲው አባላት  በሚሳተፉበት ኮንፍረንሱ  ሀገሪቱ ልታሳካ የምትችላቸውን ዕቅዶች ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዝግጁ የሆነ ኃይል የሚፈጠርበት ይሆናል ብለዋል።

ለዋናው ጉባዔ ተሳታፊዎችም የሚመርጡበትና የፓርቲ ጉባዔ የሚያስቀምጣቸውን መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ ቅድመ ውይይት የሚደረጉበት መሆኑን  ገልጸዋል።

በመሠረታዊ ፓርቲ የቅድመ ጉባዔ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኝው የኮንፈረንስ ፋይዳው በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ  አመልክተዋል።

ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ተሳትፎ የተሰጠውን የህዝብ አደራ በብቃት ለመወጣት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑንም የገለጹት ኃላፊው ፤ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይሰራልም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ከገጠማት  ፈተናዎች ለመሻገር ብሎም የፓርቲውን ራዕይ እውን ለማድረግ መደላደል ለማኖር ኮንፍረንሱ እንደሚረዳ ተመልክቷል።

ፓርቲው እስካሁን ያደረገውን ዝግጅት በሚመለከትና ቀጣይ ፈተናዎች ለማለፍ  የሚያስችል የውስጥ ጥንካሬ እና ብቃቱን በተሻለ ደረጃ የሚያረጋግጥበት እንደሆነም  አቶ አብዱጀባር አስረድተዋል።

በመጨረሻም በቅርቡ የሚካሄድ ዋናው ጉባዔ ስኬታማ ለማድረግ መላው በክልሉ የሚገኙ የፓርቲው አባላት በየደረጃው በሚከናወኑ የመሠረታዊ ፓርቲ ኮንፈረንሶች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም