የግንባታ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይገባል-ባለስልጣኑ

85

ድሬደዋ፤ የካቲት 21/2014 (ኢዜአ)፤ የግንባታ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው የህብረተሰቡን የልማት ችግሮች እንዲፈቱ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን አስገነዘበ ።
 ''ግንባታ ለሀገር አለኝታ''  በሚል መሪ ሃሳብ የኮንስትራክሽን የንቅናቄ መድረክ በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።

የባለስልጣኑ  ምክትል ዳይሬክተር አቶ ማተቤ  አዲስ እንደ ሀገር 60 በመቶ የሚሆነው በጀት ለካፒታል ፕሮጀክቶች  ማስፈፀሚያ እንደሚመደብ ገልጸው በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ከማምጣት አንጻር ክፍተት መኖሩን አመልክተዋል።

ዘርፉ ከሀገራዊ አመታዊ የዕድገት ምጣኔ /GDP/ 19 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸው ዘርፉ  ከግብርና  ቀጥሎ ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዋጋ ግሽበት፣ በአመለካከት ችግር፣ በኃላፊነት ጉድለት፣ ጥቅም መቀራመት፣ የዕውቀት ክፍተት፣ ተቀናጅቶና ተባብሮ አለመስራት የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት እንዳይጠናቀቅ የሚያደርጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

ፕሮጀክቶች በሚፈለገው  ጥራትና ፍጥነት ተገንብተው የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው  አስገንዝበዋል።

ዛሬ የተጀመረው የንቅናቄ መድረክ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፈታት የሚያስችሉ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡበት መሆኑን ጠቁመው፤  ልምድ በመለዋወጥ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው ውይይቱ በግንባታው ዘርፍ በጥራት ጉድለት፣ በሥነ-ምግባር ግድፈትና በግል ጥቅም አሳዳጅነት የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ምክረ ሀሳብ እንደሚገኝበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

መድረኩ በግዢ ፣ በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በህብረተሰብ ጤንነትና የግንባታ አፈጻጸም ችግሮች ላይ በመወያየት የግንባታ ፕሮጀክቶችን  ቁጥጥር ስራ ለማጠናከር  ግብዓት የሚገኝበት መሆኑን አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይ የፌዴራል፣ የሶማሌና የሐረሪ ክልል እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የጅግጅጋና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እንቀሳቃሾችና ሙሁራን እየተሳተፉ ነው፡፡

ለሶስት ቀን የሚካሄደው መድረክ በግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጉዳዮች ላይ የቁጥጥር ሥራን አቀናጅቶ ፕሮጀክቶች በተያዙላቸው በጀት ፣ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል የታሰበ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም