በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ከ108 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል- ባለስልጣኑ

71

ሐዋሳ፤ የካቲት 21/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ከ108 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን የደቡብ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ።

በክልሉ ህገ ወጥ የቡና ንግድና ዝውውርን ለመቆጣጠር በተከናወነ ተግባር  7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቡና መያዙ ተመላቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የስራ እድሉን የፈጠሩት በክልሉ የሚገኙ 412 የታጠበና ያልታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ናቸው።

በኢንዱስትሪዎቹ ለ92 ሺህ 221 ዜጎች የስራ እደል ለማመቻቸት ታቅዶ ለ108 ሺህ 895 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

ከስራ እድሉ ተጠቃሚዎች መካከል 62 ሺህ 392ቱ ሴቶች  መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በቡና ልማትና ዝግጅት ዘርፍ ለሚሰማሩ  ባለሀብቶች  ፍቃድና  አስፈላጊ  የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት የስራ እድሉን ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በክልሉ የቡና ልማትን ለማስፋፋት የተያዘውን ውጥን ለማሳካት ባለፉት አራት ዓመታት የቡናን የብቅለት ደረጃ ለማራዘም የሚረዱ ደረጃቸውን የጠበቁ 12 ቀዝቃዛ መጋዝኖች መገንባታቸውን አስታውቀዋል።

መጋዘኖቹ የተገነቡት በጌዴኦ፣ወላይታ፣ጋሞ፣ጎፋና አማሮ አካባቢዎች መሆኑን ጠቁመው፤ የመጋዘኖቹ መገንባት በ17 ሺህ ችግኝ ጣቢያዎች የሚከናወነውን የቡና ችግኝ ዝግጅት ውጤታማ እያደረገው መሆኑን  አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት የክልሉን የቡና ብቅለት ደረጃ በማሻሻል ከ100 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ መደረጉን  አመልክተዋል።

በተያዘው ዓመት 90  ሚሊዮን  የቡና ችግኝ  ለማዘጋጀት  ታቅዶ እየተሰራ  መሆኑን  የጠቆሙት አቶ ሬድዋን፤  እሰካሁን ከ74 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ከቡና ልማቱ የሚገኘውን ገቢ እንዲቀንስ የሚያደርገውን የኮንትሮባንድ ንግድ  ለመከላከል  ባለፉት  ሰባት  ወራት  በተከናወኑ  የቁጥጥር  ተግባራት   7 ሚሊዮን 322 ሺህ ብር ግምት ያለው ቡና መያዙን ተናግረዋል።

የተያዘው ቡና ግምታዊ ዋጋ ካለፈው ዓመት  ተመሳሳይ ወቅት  ጋር ሲነፃፀር  በ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

የቡና ልማትን ለማስፋፋት ቴክኖሎጂዎችንና የተሻሻሉ አሰራሮችን ከመዘርጋት ጎን ለጎን የተጠናከረ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

የቡናን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ ቀለጣፋ የግብይት ሥርዓት በመዘርጋት ከዘርፉ የሚኘውን ጥቅም  ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል ።

በወላይታ ሶዶ ከተማ በደረቅ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ ሰራተኛ ወይዘሮ ሽታዬ ከበደ  በቀን 75 ብር እየተከፈላቸው  በሚሰሩት ስራ ቤተሰቦቻቸውን መደጎም መቻላቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም