ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይሰራል

123

አዲስ አበባ የካቲት 21/2014 /ኤዜአ /በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም  ፋራህ፤ የፓርቲው አንደኛ ጉባኤ "ከፈተና ወደ ልዕልና" በሚል መሪ ሐሳብ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

"ብልጽግና የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ተከትሎ የመጣ ለውጥ የወለደው ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነው'' ሲሉም አብራርተዋል።

የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ዓላማን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ብልጽግና አገራዊ ለውጡን ከመምራት አንጻር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተዋል።

በተጨማሪም ፓርቲው በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እድገትና ብልፅግና እውን እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አቶ አደም ገልጸዋል።

በስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የተሰጠውን የህዝብ አደራ በብቃት ለመወጣት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመው በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይሰራልም ብለዋል።       

የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት ፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤውን ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲያካሂድ መወሰኑን አመልክተዋል።

የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የማሸጋገር ዓላማን የሰነቀ መሆኑንም አብራርተዋል።   

የለውጥ ሂደቱን በጥልቀት መገምገም፣ የተገኙ ስኬቶችን ጠብቆ ማስቀጠል፣ የታዩ ድክመቶችን ማረም እንዲሁም የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የጉባኤው ትኩረት መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚሁ ጉባኤ ላይ ፓርቲውን በብቃት የሚመሩ አመራሮች ይመረጣሉ ሲሉም ጠቁመዋል።

በጉባዔው 1 ሺህ 600 የፓርቲው አባላት በድምጽ፤ 400 የሚሆኑ ተጋባዥ እንግዶች ደግሞ ያለ ድምፅ ይታደማሉ ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ከ38 የተለያዩ አገራት የሚጋበዙ 41 የብልጽግና እህት ፓርቲ ተወካዮችም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአገር ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችም በጉባኤው ይሳተፋሉ ተብሏል።

ብልጽግና ፓርቲ ከ11 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም