በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ በእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰበት ቤተሰብ ከ500 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ተደረገ

110

ሆሳዕና፣ የካቲት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ በድንገተኛ የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰበት ቤተሰብ ከ500 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ፣ አልባሳትና የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።

የሚቶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑረዲን ሶንችላ በወረዳው የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት በተከሰተ ድንገተኛ የእሳት አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባል የነበሩ ሶስት ህፃናት ህይወት ማለፉን፣ ሁለት መኖሪያ ቤቶች፣ ከሰባት በላይ የቤት እንስሳትና የተለያዩ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን አስታውሰዋል።

አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የወረዳው አስተዳደር ጉዳት የደረሰባቸውን የቤተሰብ አባላት በማጽናናት ከጎናቸው ሆኖ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ዛሬ ከስልጤ ዞን አስተዳደርና ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር ከ500 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስና የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ከጊዜያዊ ድጋፍ ባሻገር ቤተሰቡን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ስራዎች እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድጋፉ የምግብ እህልና የአልባሳት እንዲሁም ለቤት መስሪያ የሚሆን 80 ቆርቆሮ፤ እንጨትና ሚስማር ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም