የኢትዮጵያ አየር ሃይል በቴክኖሎጂ ዘምኖና በአደረጃጀቱ ተሻሽሎ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ እየተገነባ ነው

111

የካቲት 20/2014/ኢዜአ/ አየር ሃይል በቴክኖሎጂ ዘምኖና በአደረጃጀቱ ተሻሽሎ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የአየር ኃይል አብራሪዎችና አመራሮች፣ ቴክኒሻኖችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች የተውጣጡ አባላት የሽልማት፣ ማዕረግ ሹመትና ዕድገት ሰጥቷል።

ከሽልማቶች መካከልም ከአንደኛ እስከ 3ኛ የዐውደ ውጊያና የምርጥ አመራር ጀግና ሜዳይ ሽልማቶች ይገኝበታል።

የሽልማትና ማዕረግ ዕድገት ከተሰጣቸው የአየር ሃይል አባላት መካከልም 92 ከፍተኛ መኮንኖች፣ 42 መስመራዊ መኮንኖች፣ 460 ባለሌላ ማዕረግተኞች ይገኙበታል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ አየር ኀይል የአገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ከትናንት እስከ ዛሬ አኩሪ ገድል እየፈፀመ የዘለቀ ስመ ገናና ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ለ27 ዓመታት ተቋሙን በማዳከም ደባ ቢፈፀምም ከ3 ዓመታት ወዲህ በተሰራው ስራ ዘመን ተሻጋሪ ተቋም ለመገንባት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኀይልን በማዘመን፣ በቴክኖሎጂ በማገዝና አደረጃጀቱን በማሻሻል ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም የማድረግ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የአገርን ሕልውና በመታደግ ረገድ አኩሪ ገድል መፈፀሙን አስታውሰው በዚህ ሂደት ለተሳተፉ ጀግኖችና የስራ ክፍሎች እውቅና መሰጠቱን ገልፀዋል።

ለጀግኖች የሰራዊቱ አባላት የተሰጠው ዕውቅና ለቀጣይ የላቀ ግዳጅ አፈፃፀም የሚያዘጋጅ መሆኑንም ዋና አዛዡ ተናግረዋል።

ለአየር ሃይሉ የሚመጥን ብቃትን መሰረት ያደረገ የሰው ሃይል ምልመላና ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው፣ በዕለቱ የተመረቁ ቴክኒሻኖችና ኤር ፖሊስ አባላት የዚህ ውጤት ማሳያ ናቸው ብለዋል።

የአየር ኃይል አካዳሚ በአቪየሺን ቴክኒሻኖች በሙያው ብቁ የሚያደርጓቸው በተለያዩ የንድፈ ሀሳብና የተግባር  ትምህርቶችን ወስደው መመረቃቸውንም ነው የገለፁት።

በወሰዱት ትምህርት መሰረት ተመራቂዎች አገርና ወገንን በፅናት፣ በጀግንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም