የእርሻ መሣሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካ ተገንብቶ ለአገልገሎት በቃ

68
አዳማ ነሀሴ 27/2010 በሻሸመኔ ከተማ 150 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ኬኛ የተሰኘ የእርሻ መሣሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቃ። ፋብሪካውን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ትናንት መርቀዋል፡፡ በምርቃ ስነ ሥርዓቱ ወቅት ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት የክልሉ መንግስት ባለሀብቶችንና ባለሙያዎችን በማሳተፍ  የጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ  አጠናክሮ ይቀጥላል። "በተለይ በአርሶ አደሩ ጉልበት ላይ የተመሰረተው የግብርና ልማት የሚፈለገውን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ አዳገች ነው "ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነቱን በማሳደግ ተጠቃሚነቱ ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ የፋብሪካው መገንባት የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው አርሶ አደሩና ወጣቶች ምርቱን በስፋት እንዲጠቀሙ  መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴና የምጣኔ ሃብት እድገት ከዳር ለማድረስ ባለሀብቱ፣ምሁራንና ወጣቶች ያልተቆጠበ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ለማ ፋብሪካው ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረታቸውን ባለ 75 የፈረስ ጉልበት የሆኑ  60 ትራክተሮች በ60 ኢንትርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች አስረክበዋል። ወጣቶቹ ትራክተሮቹን እንዲረከቡ የተደረገው በ46 ነብጥ 3 ሚሊዮን ብር የብድር ገንዘብ ነው፡፡ የፋብሪካው መስራችና የቦርድ አባል አቶ ጉደታ ገላልቻ በበኩላቸው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተገነባው ፋብሪካው  በ10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው ከአሜሪካው ጆን ዳር ኩባንያ ጋር በሽርክና የሚሰራ መሆኑን ጠቁመወ በሙከራ ደረጃ በቀን 25 ትራክተሮችን በማምረት ላይ  እንደሚገኝ ተናግረዋል። "በአሁኑ ወቅት ቀሪ መገጣጠሚያ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውሰጥ እየገቡ በመሆኑ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን እስከ 100 ትራክተሮችን ያመርታል "ብለዋል። ፋብሪካው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ከቴክኒክና ሙያ ለተመረቁ 80 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩንም ለማወቅ ተችሏል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ትናንት በሻሸመኔ ከተማ እየተገነባ ያለውን ግዙፍ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም