በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 16 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

83

ነገሌ ፤ የካቲት 19.2014( ኢዜአ) በምዕራብ ጉጂ ዞን ስድስት ወረዳዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 16 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህልና የእንስሳት መኖ ድጋፍ ተደረገ፡፡

ትናንት በዞኑ ከተማ ቡሌ ሆራ   በመገኘት ድጋፉን ያደረጉት  የሰበታ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክና የፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን ናቸው።

ድጋፉን የተረከቡት የምዕራብ ጉጂ ዞን አደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት  ሀላፊ አቶ እዮብ ዘሪሁን፤  የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት እየተደረገ ያለው ድጋፍና ትብብር የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡

 3 ሺህ 800 ኩንታል የበቆሎና የስንዴ እህል እንዲሁም አልሚ ምግብ ፣   250 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣  4 ሺህ 400 እስር  የእንስሳት መኖ  ከድጋፉ ውስጥ ይገኙበታል፡፡

ድጋፉ በዞኑ መልካ ሶዳ፣ ዱግዳ ዳዋ፣ ገላና፣ አባያ፣ ሱሮ በርጉዳና ቡሌ ሆራ ወረዳዎች በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች የሚከፋፈል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ለዞኑ አርብቶ አደሮች ባለፈው ሳምንት ከወሊሶ ከተማ አስተዳደር ስድስት መቶ ኩንታል በቆሎ ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡

በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ የቡሌ ሆራ ቅርንጫፍ ሀላፊ አቶ ብርሀኑ አሰፋ፤ ባንኩ ከሚሰጣቸው አገልግሎት መካከል አንዱ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ነው ብለዋል፡፡

ልማትና እድገት ከህዝብና ከሀገር ጋር በመሆኑ ባንኩ በድርቁ ምክንያት ለምግብ እህልና እንስሳት መኖ እጥረት ለተቸገሩ ወገኖችን የሚያደርገውን ድጋፍ ወደፊትም እንደሚቀጠል አስታወቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም