የአርሶ አደሮችን የግብይት ሰንሰለት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው

380

ባህር ዳር የካቲት 19/2014(ኢዜአ) የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሮችን የግብይት ሰንሰለት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአማራ ክልል የግብርና  “ውል ”  አመራረት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በባህር ዳር ከተማ  እየተካሄደ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ በውይይቱ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤  የግብርና  “ውል” አመራረት የአሰራር ዘዴ ከማምረት እስክ ግብይት ያለውን ችግር በዘላቂነት ይፈታል።

አርሶ አደሩ ከማምረት በዘለለ በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ አሰራሩ ችግሩን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።

በተለይም መሬት ያለውን አርሶ አደር ሃብት ካለው ከባለሃብት ጋር በውል በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን የግብዓትና የቴክኖሎጂ አቅርቦት እጥረት በማስወገድ ምርታማነትን እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።

በዚህም ጥራቱን የጠበቀ ምርት በብዛት በማምረት ለውጭ ገበያና ለኢንዱስትሪዎች ከማቅረብ ባለፈ  የአርሶ አደሩን የገበያ ችግር በቋሚነት እንደሚፈታ ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።

አማራ ክልልን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በልማዳዊ መንገድ ይከናወን የነበረውን አሰራር በህግ አግባብ ለማከናወንም  ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው በበኩላቸው፤ የግብርና ምርት ውል አመራረት ዘዴ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለባለሃብቶችና ለአርሶ አደሮች ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ግብዓትና ቴክኖሎጂ በማግኘት ጥራት ያለው ምርት በብዛትና ጥራት አምርቶ  ለውጭ ገበያ በተሻለ መጠን ለማቅረብ ያስችለዋል ብለዋል።

”የክልሉ አርሶ አደር ዓመቱን ሙሉ በሚባል ደረጃ ይለፋል” ያሉት ሃላፊው፤ በልፋቱ ልክ ግን በግብርና ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የግብርና ” ውል ” አመራረት   የአሰራር ሰንሰለት በአርሶ አደሩና በተጠቃሚው መካከል ያለውን ደላላ በማስቀረት አምራቹ በቀጥታ ለኢንዱስትሪዎችና ተደራጅቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

ክልሉ ባለፈው ዓመት በአሰራሩ በ13 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 130 ሺህ ኩንታል  አኩሪ አተር አምርቶ ለውጭ እንዲያቀርብ ድጋፍ መደረጉን ዶክተር ሃይለማርያም አመልክተዋል።

ካለፈው ልምድ በመነሳትም በቀጣይ አሰራሩን በሁሉም አካባቢዎች በማስፋፋት ገበያውን፣ ኢንዱስትሪውንና የውጭ ምንዛሪውን ለማረጋጋት ይቻላል ብለዋል።

‘’የግብርና ምርት ውል አመራረት በሃገሪቱ ሰላማዊና ዘላቂ ኢንቨስትመንት እንዲካሄድ ያግዛል’’ ያሉት ደግሞ በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ምርት ውል ቡድን አስተባባሪ አቶ ደረጀ አበበ ናቸው።

የአሰራር ዘዴው የሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና የውጭ ንግዱ የማይቋረጥ የምርት አቅርቦት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአሰራር ዘዴው በሃገሪቱ በአኩሪ አተር፣ በቡና፣ በማሾ፣ በሻይና በሰብል እንዲሁም በሌሎች የግብርና ልማት ከ80 የሚበልጡ ባለሃብቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአሰራር ዘዴው በህግ ተደግፎ እንዲወጣ በማድረግምም በውል ሰጭና በውል ተቀባይ መካከል ከፍተኛ መተማመን በመፍጠር ዘርፉን በፍጥነት ለማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው የውይይቱ መድረክ የአማራ ክልልና የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ከባህርዳር ዘግባል።