የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

132

የካቲት 19/2014 /ኢዜአ/ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት የሰዎች  ለሰዎች  ድርጅት በኢትዮጵያ ስራ የጀመረበትን 40ኛ ዓመት ባከበረበት መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በመርሃ-ግብሩም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚህን ወቅት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ባለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ላከናወናቸው በጎ ስራዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተለይ በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎች እራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ድርጀቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፤ ይህም ለሌሎች ድርጅቶች አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በቀጣይ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የሰዎች ለሰዎች ድርጅቱ እስካሁን ባለው ሂደት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

በርካታ ዜጎችን አስተምሮ ለትልቅ ደረጃ እንዳበቃ ገልጸው፤ ድርጅቱ ላበረከተው አስተዋጽኦም የእውቅና ስጦታ አበርክተዋል፡፡

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉና የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመደገፍ 2 ሚሊዮን ዮሮ መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በጀርመናዊው ካርል ሄንዝ በም የተመሰረተው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ባለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ከ461 በላይ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከ500 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉም ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም