በምሥራቅ ወለጋ ዞን ወደ 231 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጁ

460

ነቀምቴ የካቲት 19/2014 /ኢዜአ/ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በመጪው የክረምት ወራት የሚተከሉ ወደ 231 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ የግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡
የጽህፈት ቤቱ የተፋሰስ ልማትና የደን ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ደሣለኝ በለታ እንደገለጹት ችግኞቹ የተዘጋጁት  በዞኑ 17 ወረዳዎች ለማዘጋጀት ከታቀደው ከ368 ሚሊዮን ባለይ ችግኝ ውስጥ ነው።

በዞኑ ችግኞቹ ለተከላ የተዘጋጁት ከ2 ሺህ በሚበልጡ የመንግሥት፣ የፕሮጀክት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት እና በአርሶ አደሮች  መሆኑንም አመልክተዋል።

በዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በቀሪ ጊዜያት ችግኞችን የማዘጋጀቱ ሥራ በቀጣይነት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በዞኑ የተዘጋጁት ችግኞች የደን ዕፅዋት፣ የእንስሳት መኖ፣ የፍራፍሬና የቀርከሃ ዛፎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ችግኞችም 89ሺህ 876 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚተከሉም አስረድተዋል።

በተለይም በዞኑ በእርሻ ሥራ ምክንያት ዝርያው እየጠፋ የሚገኘውን የቀርከሃ ዛፍ መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ የችግኝ ዝግጅት በየዓመቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

በተፈጥሮ የሚገኘውም የቀርከሃ ዛፎች በያለበት ተከልሎ አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑንም የቡድን መሪው አመልክተዋል፡፡

በዞኑ ሳሲጋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ በሊና በበኩላቸው በወረዳው በ131 የመንግሥትና የግል የችግኝ ጣቢያዎች ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን  ተናግረዋል።

የሳሲጋ ወረዳ መሬቱ ክፉኛ በምስጥ የተጎዳ በመሆኑ በአፈር አሲዳማነት ምክንያት እህል ማብቀል ከማይችልበት ደረጃ መድረሱን ኃላፊው አስታውሰዋል።

በየዓመቱ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እና ችግኞችን በመትከል አከባቢው አሬንጓዴ ለብሶ   የወረዳው የሥነ ምህዳር ተለውጦ የአፈር ለምነት ተጠብቆ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በበጋ ወራት ይደርስበት ከነበረው የእንስሳት መኖ ችግር በመላቀቅ እንስሳትን በማርባትና በማድለብ ከፍተኛ ጥቅም እያገኘ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡