ደምዶሎ ዩንቨርሲቲ ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው

ግምቢ የካቲት 19/2014 (ኢዜአ) ደምዶሎ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ 187 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን አስታወቀ
ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን እየሰጠ የሚገኘው የነጋሶ ጊዳዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚል በከፈተው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው።

በዚህም ባለፈው ዓመት  በቀለም ወለጋ ዞን   ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የስምንትኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ነጥብ ያመጡትን በማወዳደር የተቀባሏቸው ተማሪዎች በአዳሪነት እያስተማሩ መሆናቸውን  

የዩኒቨርሲቲው  የአስተዳደር  ምክትል ፕሬዚዳንት   ዶክተር ሙሉጌታ ተሰማ ገልጸዋል።

ዪኒቨርሲቲው የተቀባላቸውን ተማሪዎች  የሚያስተምረው እስከ 12ኛ ክፍል በጀት መድቦ  ወጪያቸውን በመሸፈን  መሆኑን  አመልክተዋል።

ይህም ዩኒቨርሲተው ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ከታች ጀምሮ በመስጠት በሀገር ውስጥና በውጭ ተወዳዳሪ የሆነ ዜጋን  ለማፍራት  የበኩሉን  ለመወጣት መሆኑን ዶክተር ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የነጋሶ ጊዳዳ ሁለተኛ ደረጃ ልዩ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር መምህር ጫሊ ለገሰ ፤ትምህርት ቤቱ ከዞኑ ተወዳዳሪና በትምህርታቸው ከፍተኛ ነጥብ ያላቸውን 187 ተማሪዎች አወዳድሮ በመቀበል እያስተማረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ ብቁ መምህራን፣  ቤተ መጻህፍትና ሌሎችንም የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላቱን አመልክተዋል፡፡

በመማር ላይ ከሚገኙት ተማሪዎች መካከል ሁንዱማ ጫላ በሰጠው አስተያየት፤  በትምህርት ቤቱ እየተሰጣቸው የሚገኘው ትምህርት ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው ገልጿል።

ለተሻለ ውጤት ለመብቃትም ትምህርቱን በትኩረት እየተከታተለ እንደሚገኝም  ተናግሯል።

ተማሪ ሜቲ መንግስቱ በበኩሏ፤  በትምህርት በቱ ተወዳደሪና ጎበዝ ተማሪዎች ስለሚማሩ የርስ በርስ ፉክክር መኖሩን ገልፃለች።

ወደፊትም ዶክተር ለመሆን እንደምትፈልግና ይህንንም ለማሳካት   በትጋት በማጥናት ትምህርቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ያመለከተችው፡፡

ከነበረችበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ባገኘችው ውጤት ተወዳድራ በማለፍ ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸው ዕድል ተጠቃሚ መሆኗን የተናገረችው ደግሞ ተማሪ ኡሜራን ገመቹ ናት።  

ትምህርተ ቤቱ ለመማር ማስተማሩ ስራ  የተሟላ በመሆኑ ወደፊት በሀገር  ደረጃ ተወዳዳሪ ተማሪ  ለመሆን ጠንክራ እያጠናች መሆኗን ገልፃለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም