በኦሮሚያ ክልል የኀብረተሰቡን ኑሮ የሚለውጡ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው

140

የካቲት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የኀብረተሰቡን ኑሮ የሚለውጡ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

በፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የ'ኬኛ ቢቬሬጅ ኢንዱስትሪ' እና የአምቦ-ጉደር አስፋልት መንገድ ግንባታን ጎብኝቷል።

ፕሬዚዳንቱ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ከሶስት ዓመት ወዲህ የኀብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እየገቡ ነው።

በዚህም በማዕድን፣ በሞተር መገጣጠሚያ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰሩ 16 ኩባንያዎች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል በ'ኬኛ ቢቬሬጅ ኢንዱስትሪ' ስር የሚገነባው 'የኬኛ ቢራ ፋብሪካ' በተሻለ የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ፋብሪካውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኬኛ ቢቨሬጅ ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ አምሳል መገርሳ በበኩላቸው የፋብሪካው ግንባታ በተቀመጠለት እቅድ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ ወደ ምርት እንደሚገባ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በክልሉ ፕሬዚዳንት የሚመራው ልዑክ ጉብኝት ያደረገበት ከአምቦ-ጉደር የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

ሁለቱን ከተሞች የሚያገናኘውና 19 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ሲሆን፤ ግንባታውን የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አስመራ አቤቤ የግንባታው አፈጻጸም 20 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ቢያዝለትም ከካሳ ክፊያ ጋር በተያያዘ የግንባታ ሂደቱ መጓተቱን አንስተዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ከትራንስፖርት መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ አስታውሰው፤ የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ በተስፋ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም