ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተን አሸባሪውን ሸኔ እንታገላለን

60

ግምቢ፣ የካቲት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሸባሪውን ሸኔን የጥፋት ድርጊት እስከ መጨረሻ ለመመከት ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በፅናት እንደሚታገሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡


የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኦነግ ሸኔን በተመለከተ እንደገለጹት፤ ቡድኑ የፖለቲካ ግቡ ምን እንደ ሆነ የማይታወቅ እና ለሰው ልጆች ክብር የሌለው ነው።

ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ቡድኑ የሀገርና የሕዝብ ጠላት መሆኑን ገልጸው፤ ከመንግሥት ጎን ሆነው በፅናት እንደሚታገሉት ተናግረዋል።

የአካባቢያቸውን ሰላም በማወክ ንጹሃንን በግፍ እየገደለ የሚገኘው ሸኔ፤ "ዓላማ ቢስ እና አሸባሪ" በመሆኑ እኩይ ዓላማውን ለማምከን ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በኦሮሞ ስም ኦሮሞዎችን ሲያሰቃይ የኖረው ዓላማ የሌለው አሸባሪው ሸኔ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ እንደሆነም ተናግረዋል።

ቡድኑ ለህዝብ የሚጠቅም ዓላማ የሌለው በመሆኑም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በመታገል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ሸኔ ምንጊዜም የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ነው" የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የሽብር ቡድኑ አርሶ አደሮችን በግፍ ሲገድል፣ ሲዘረፍና ሲያሰቃይ እንደነበር ተናግረዋል።

የሸኔን ሽብር ድርጊት ለማስቆም በሚደረገው ሁሉ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ህዝቡ ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ በአሸባሪው የሸኔ ቡድን የጥፋት ድርጊት መማረሩንም ጠቁመዋል።

የዞኑ ሕዝብ ሰላሙን ለመመለስም በተቻለው መጠን ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አሸባሪውን ሸኔን ለመደምሰስ የበለጠ መትጋት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ  አቶ ሙላቱ ዲንሳ በበኩላቸው አሸባሪው ሸኔ በዜጎች ላይ ግፍና መከራ እያደረሰ እንደሆነ ተናግረዋል።

ህዝቡ በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በመደራጀት የአሸባሪውን ሸኔ የሽብር ድርጊት ለማምከን እየተፋለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዞኑ ሕዝብ ለፀጥታ አካላት ትክክለኛውን መረጃ በመስጠትና አስፈላጊ ትብብር በማድረግ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍንም እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጠልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም