ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል-ዶክተር ሊያ ታደሰ

72

ሐረር ፤ የካቲት 18 ቀን 2014(ኢዜአ) በሀገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሐረር ከተማ ከ270 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን የካንሰር ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ከሐረር ባለፈ ለምስራቅ ኢትዮጵያ የጨረር ህክምና በመስጠት  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

ይህም  ከጥቁር አንበሳና ጅማ ሆስፒታሎች ቀጥሎ ሶስተኛው ማዕከል መሆኑን  ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና  ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  ሚስራ አብደላ በበኩላቸው፤ በክልሉ የጤና ተደራሽነት እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማጎልበት በተከናወነው ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተለይ ከክልሉ አልፎ ለአጎራባች አካባቢዎች ጭምር የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል።

የማዕከሉ ስራ መጀመር በተለይ ህክምናውን ለሚፈልጉ ዜጎች እፎይታን የሚሰጥ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ፤   በተለይ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው ህዝብ የካንሰር ህክምና አገልግሎት ለማግኘት ሲደርስበት የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀር ነው የተናገሩት፡፡

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  በህክምናው ዘርፍ ለሀገር እና ለህዝብ የሚጠቅም  በርካታ የአገልግሎት እና የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው  የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንግስቱ ኡርጌ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው  ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ በአካዳሚክና በአገልግሎት ዘርፍ   ሁለተናዊ  እድገት በማሳየት ለምስራቅ ኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተመረቀው የካንሰር ህክምና  ማዕከል ከጤና ሚኒስቴርና ተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለማዕከሉ ግንባታ በዩኒቨርሲቲው ከ70 ሚሊየን ብር በላይ፤  የጤና ሚኒስቴርና አጋሮቹ የህክምና መሳሪያዎች ግዢ 200 ሚሊየን ብር ወጪእንደተደረገበትና  በቀን ከ60 በላይ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተመልክቷል።

ሐረር ከተማ በሚገኘው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ህይወት ፋና ልዩ የማስተማሪያ ሆስፒታል የተገነባው የካንሰር ህክምና  ማዕከልን  የጤና ሚኒስትሯና የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ ሌሎችም   የፌዴራልና  የክልል እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ከሐረር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም