የካማሺ ዞንን ሠላም በዘላቂነት ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው

65

አሶሳ ፤ የካቲት 17 / 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የካማሺ ዞንን ሠላም በዘላቂነት ለመመለስ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ በማዋቀር በትኩረት እተሠራ መሆኑን የክልሉ ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ካማሺ ዞን እምነበረድ፣ ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚውል ሰፊ ድንግል መሬት እና የበርካታ ወንዞች መገኛ ነው፡፡

አሸባሪው ህወሃት ከለውጡ በፊት በኢንቨስትመንት ሽፋን የዞኑን የተፈጥሮ ሃብት እንደልቡ ሲመዘብር  እንደነበር ለኢዜአ  የገለጹት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ለውጡን ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ እና ባለሃብቶች የተፈጥሮ ሃብቱን በህጋዊ መንገድ ማልማት እንደጀመሩ ጠቁመዋል።

ይህ ሁኔታ ያልተመቸው የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተላላኪዎቹን በማቀናጀት በተለይ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የዞኑን ሠላም ማወኩንና በዚህ የተነሳ የንጹሀን ህይወት ሲያልፍ፣ በርካቶች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን እንዲሁም ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የካማሺን ሠላም ወደ ቀደመ ሁኔታው ለመመለስ በቅርቡ የዞኑን አስተዳደር እንደገና ከማዋቀር ጀምሮ የተሻለ አመራር ሊሰጡ በሚችሉ  አካላት መተካቱን አስታወቀዋል፡፡

በዞኑ ጉዳት የደረሰባቸው የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማትን ማጠናከር ሌላው የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሠራ የሚገኘው ጉዳይ እንደሆነ ያመለከቱት ምክትል ሃላፊው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የዞኑን ጉዳይ በቅርበት በመከታተል በየደረጃው ካሉ  የዞኑ አመራሮች ጋር ጠንካራ ግምገማዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዞኑ የሃገር ሽማግሌዎችን፣ ታዋቂ ሰዎች እና የሃይማት አባቶችን ያካተተ ህዝባዊ የውይይት መድረኮችም እንዲሁ፡፡

ለተፈናቃዮች የሰብዓዊ ድጋፍና ለነዋሪው ደግሞ ሸቀጣ ሸቀጦች እንዲደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ዞኑ በሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ልዩ ሃይል ጠንካራ ጥበቃና  የዞኑን ሚሊሻ በማሰልጠን ጸጥታ አስከባሪዎችን እንዲደግፉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ የጸጥታ ችግር እንዲፈጠር ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ተለይተው  በፍርድ ቤት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንና የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን በመጠገን ትምህርትን እንደገና ለማስጀመር የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የዞኑን  ሠላም የመመለሱ ስራ በተለይም ከአጎራባች ኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል መንግስት ጋር  በቅንጅት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ ጻፊዮ በበኩላቸው በእያንዳንዱ ቀበሌ የውይይት መድረክ በማካሄድ ችግሮችን በመለየት እርቀ ሠላም የማውረድ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ካማሺ ዞን ወደ መረጋጋት እየመጣ መሆኑን ገልጸው፤ ሰላምን አስተማማኝ ማድረግ የመንግስት ብቻ ባለመሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግ አቶ ብጅጋ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም